
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተፈናቅለው በባሕርዳር ከተማ ዘንዘልማ ቀበሌ ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል ያደረሰው ግፍና በደል በመላ ኢትዮጵያ የደረሰ ነው ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ አሸባሪ ቡድኑን መላ ኢትዮጵያዊያን ተረባርበው በመቅበር ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው መመለስ እና ማቋቋም እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት፡፡ ዛሬ የተደረገው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የምግብና የአልባሳት ድጋፍም ከተማ አስተዳደሩ ከተፈናቃዮች ጎን መሆኑን ለማሳየት እንደሆነ ነው ያብራሩት።
ከንቲባ አዳነች ተፈናቃዮች ዛሬ በጊዜያዊ መጠለያ ብትኖሩም ከድል በኃላ ወደ ቀያችሁ እንደምትመለሱ አንጠራጠርም ብለዋል። ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚደረገው ሥራም እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ርእስ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ በፊት በሽብር ቡድኑ ከተፈናቀሉ ወገኖች ጎን በመሆን አጋርነቱን አሳይቷል ብለዋል። ዛሬም ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። ክልሉ ከሁሉም የጸጥታ ኀይሎችና ከሕዝቡ ጋር በመሆን አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽብርተኛውን ቡድን ለመደምሰስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ ፦ አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m