ጠላት ከደጅህ መጥቶ እንቅልፍ የለምና ነጻነትህን በጠንካራ ክንድህ አስከብር፡፡

217

ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ የአማራ አደረጃጀቶችና ግለሰቦች ጥምረት በመፍጠር በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ በሚል በአማራ ሕዝብ ላይ በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳትም ጥምረቱ የአማራ የቀውስ ጊዜ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ስርዓት ዘርግቶ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሲስተር ሙሉ ያየህይራድ እንዳሉት በተሠራው ሥራ ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የተሰበሰበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 12 ሚሊዮን ብር ደሴ፣ 10 ሚሊዮን ብር ደግሞ ጎንደር ለሚገኙ ተፈናቃዮች ተመድቧል፡፡ ለወላድ እናቶች፣ ለሕጻናት፣ ለነብሰ ጡሮች፣ ለአቅመ ደካሞች እና ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ በመስጠት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን አድርጓል፤ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ዶክተሮችንም አሰማርቷል፡፡

በአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች የተደፈሩ ሴቶች ለደረሰባቸው የጤና እና የአዕምሮ ቀውስ ሕክምና እና የሥነልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ እየተሠራ እንደሆነም ነው ሲስተር ሙሉ የተናገሩት፡፡

በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በኖርዌይ፣ በስዊድን፣ በኔዘርላንድስ፣ በጣልያን እና በሌሎች ሀገራት የተሰባሰቡ አደረጃጀቶች በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል እንዲቆም እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘበው ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ትብብር በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚሠሩ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በማንነታቸው ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ጥምረቱ ሀብት ለብክነት እንዳይጋለጥና ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ በአንድ ቋት እንዲሰበሰብ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው፡፡ ሕዝቡ የሚደርስበትን ግፍና በደል በራሱ አቅም እንዲመክት የማንቃት፣ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ እንዲሁም የጥናትና ምርምር ሥራም እያከናወነ ነው፡፡

በሰሜን አሜሪካ የአማራ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንትና በኮሎራዶ የአማራ ማኅበር ሰብሳቢ ጌታቸው መኮንን ኮሚቴውን ወክለው የተሰበሰበው ሀብት በምን መልኩ እየተሰራጨ እንደሆነ ለመከታተል ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ አንድ ወር ሆኗቸዋል፡፡ ሀገር ውስጥ ባለው ኮሚቴ አማካኝነት ርዳታው በቀጥታ ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንጻር የአማራ የቀውስ ጊዜ ሀብት አሰባሰብ ሂደት አናሳ በመሆኑ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መድረስ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፤ ይህንንም ለወከሏቸው አካላት ማሳወቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ጥምረቱ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት እስከማቋቋም የሚዘልቅ የድርጊት ዕቅድ አውጥቶ ነው እንቅስቃሴ የጀመረው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው የቤት ሥራ ከባድ ነው ይላሉ አቶ ጌታቸው፡፡ የተፈናቀለው አርሶ አደር ወደ ቀየው ሲመለስ የሚያርስበት በሬ የለም፤ ጠላት በጥይት ገድሎበታል፤ በግና ፍየሉን አርዶ በልቶበታል፣ የሚጠለልበት ጣሪያ የለውም ቤቱ ተዘርፏል፤ በእሳትም ተቃጥሏል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ሀብት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡ የአማራ የቀውስ ጊዜ ሀብት ማሰባሰቢያ ስርዓት በየትኛውም ሀገር ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ክፍት መሆኑን በማንሳት ፍላጎት እና አቅሙ ያላቸው እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡

በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የተፈናቃዮች መረጃ አያያዝ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ ነበር ብለዋል፡፡ የቢሮክራሲ ችግሮች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በአማራ እና አፋር ሕዝብ ላይ በተከፈተው ጦርነት ሕዝቡ ለከፍተኛ ቀውስ መጋለጡን ያነሱት አቶ ጌታቸው ችግሩ ለሁለቱ ክልል ሳይሆን በሀገር ሕልውና ላይ የተደቀነ አደጋ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤቱን እንደሚያንኳኳ በመረዳት በአንድነት መንቀሳቀስና ችግሩን በማያዳግም ደረጃ መቀልበስ ይገባል፡፡ ሁሉም ዜጋ ችግሩን እኩል የመጋፈጥ ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት፡፡ ‹‹ዲያስፖራው ማኅበረሰብም እንደ አዲስ መነሳት ያለበት በዚህ ጊዜ ነው፣ ኢትዮጵያን የሚያድን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የአፋር እና የአማራ ክልል ሕዝብን ለማዳን የሚነሳበት ጊዜ አሁን ነው›› ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብም ልጁን፣ እናቱን፣ አባቱን፣ ሚስቱን፣ እህት እና ወንድሙን እንደማጣት የሚያስከፋ ነገር የለም፣ ጠላት ከደጁ መጥቶ የሰላም እንቅልፍ የለም እና ነጻነቱን በጠንካራ ክንዱ እንዲያስከብር አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሽብርተኛው ትህነግን እየተፋለመ ላለው የመከላከያ ሠራዊት ከ150 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረጉ፡፡
Next articleአሸባሪው ሕወሐት መሣሪያዎቹን ሲጨርስ ምላሱን መተኮስ ጀምሯል!