
አሸባሪው የትህነግ ኃይል በ27 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ አያሌ ዜጎች ላይ መከራና እንግልት በማድረስ የሀገርን ሐብት ሲዘርፍና ሲያዘርፍ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ትህነግ በውስጥና በውጭ እንዲሁም በሐሳብ በተደረገው የተቀናጀ ትግል የሀገራችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚመጥን ሐሣብ የማመንጨት አቅም መንምኖበት በ2010 ዓ.ም ከሥልጣን ተወገደ፡፡ ይህ ትግል ያስገኘው ድል ለሀገራችንና ህዝባችን በተስፋ የተሞላ አዲስ ምዕራፍ መክፈት ችሏል፡፡
ይሁን እንጂ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በጠመንጃ የራሱ አድርጎ ከነበረው የመንግሥት ሥልጣን በህዝባዊ ተቃውሞና በመድረክ ትግል ቢነጠቅም፣ በሥልጣን ዘመኑ የዘረፈውን ሐብት በመጠቀም ላለፉት አራት ዓመታት በሀገራችን ረብሻ እና ግጭቶችን በመፍጠርና በማስፋፋት ሀገራችንን ለማፍረስ ያለውን ዓላማ ለማሳካት አቅሙን ሁሉ አሟጦ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
እንደ ሸኔ ካሉት የሽብር ኃይሎች ጋር በመመሳጠር የብሔርና የሃይማኖት ግጭቶችን በመፍጠር የአያሌ ዜጎችን ህይወት ለቀውስ ዳርጓል፡፡ ብዙዎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለሥነ-ልቦና እና የንብረት ጉዳት አጋልጧቸዋል፡፡
የትህነግ የሽብር ኃይል ግጭትና ሁከት በመፍጠር የዜጎችን ህይወት ለመከራ ከማጋለጥ አልፎ፣ በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን የሰሜን ዕዝ ላይ ባደረሰው የክህደት ጥቃት የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ ሠላምና መረጋጋት ለአደጋ አጋልጦ ነበር፡፡
ይህ የሽብር ቡድን በቅርቡ በአማራ እና በአፋር ህዝቦች ላይ ባደረሰው ወረራ፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ከመኖሪያ ቀያቸውና ከሐብት ንብረታቸው በማፈናቀልና በመዝረፍ፣ ሴቶችን በመድፈር፣ ዘግናኝ ግድያዎችን በመፈጸም ተወዳዳሪ የሌለው ጭካኔ አሳይቷል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ኃይል ከተላላኪዎች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለመበተን የፎከረበትን ህልሙን ለማሳካት፣ ያለውን ኃይል ሁሉ ማሰማራት ብቻ ሳይሆን ከሀገራችንን ጠላቶች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ከማንም ጋር የማይደራደር የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይለያይ፣ የትህነግ የሽብር ቡድን የሰነዘረበትን እኩይ ጥቃት በአንድነት እየቀለበሱ ይገኛሉ፡፡
የክልላችን ህዝብም ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ‹‹ለሀገራችን እስከ ነፍሳችን›› በማለት የሚያስፈልገውን ሁሉ እየሰጠ ነው፡፡
ትህነግ ትናንት እንደለመደው የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች በትናንሽ ልዩነቶች በመለያየት በመካከላቸው ጥርጣሬን ፈጥሮ እየገዛ ነበር፡፡ ዛሬም አንድነታችንን ለማዳከም የውሸት ፕሮፖጋንዳ ማምረትና ማሰራጨት ቀጥሎበታል፡፡
በተለይም በኦሮሞ ህዝብና በአማራ ህዝብ መካከል ያለውን ወንድማማችነት ለማዳከም ያልተበተበ ሴራ፣ ያልተሰራ ፕሮፖጋንዳ፣ ያላሰራጨው የጥላቻ መርዝ አልነበረም፡፡
ይሁን እንጂ የኦሮሞ ህዝብና እና የአማራ ህዝብ እንደ ትናንቱ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ወድቀው በመነሳት ኢትዮጵያን እንደገነቧት፣ ዛሬም የአንድነቷ እና የህዝቧ ጸር የሆኑ፣ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ለአደጋ የሚያጋልጡ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ለመቀልበስ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በአንድነት ቆመው እየተፋለሙ ይገኛሉ፡፡
የኦሮሞ ህዝብና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የትህነግ አሸባሪ ቡድንን ለመደምሰስ ሰሞኑን እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ የሚስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ በመስጠት፣ የትህነግ ተላላኪ የሆነውን ሸኔ ከክልላችን ለማስወገድ ህዝብና መንግሥት ተባብረው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
የክልላችን ህዝብ እንደ ትናንትናው አንድነታችሁን ጠብቃችሁ፣ በውጭና በውስጥ ኃይሎች ያስመዘገባችሁትን ድል ዛሬም በአንድነት የሀገራችን ጸር የሆኑ ኃይሎችን በማስወገድ አገራችንን ብልጽግና እንደምታሳኩ ጥርጥር የለውም፡፡
በመጨረሻም የኦሮሞ ህዝብ በክልላችን ለብዙ ዘመናት በሰላም ከኖሩ ብሔር በሔረሰቦች ጋር በመተባበር በህዝቦች መካከል ጥርጥር የሚረጩና ጥላቻን የሚያሰራጩ የጥፋት ኃይሎችን በመታገል፣ ለክልላችን ልማት በመደማመጥና በአብሮነት መስራት ከየትኛውን ጊዜ በላይ አሁን አስፈላጊ ነው፡፡
በተለይም ከክልላችን የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ከአካባቢያችሁን ሰላምና መረጋጋት በንቃት እንድትጠብቁና ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን እያደረጋችሁ ያለውን እርዳታ እንድትቀጥሉበት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት