ክተት፣ ዝመት፣ መክት፣ አንክት!

301

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሐምሌ 5/2013 ዓ.ም በአማራ ሕዝብ ላይ መጠነሠፊ በሆነ መልኩ ዳግም ወረራ የፈፀመው አሸባሪው ትህነግ ሁሉንም ነገር ማውደሙን ቀጥሏል። በሰሜን ወሎ፣ ዋግኸምራ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ አሁን ደግሞ ደቡብ ወሎ አካባቢዎችን በመውረር የበርካቶችን ህይወት አጥፍቷል፣ ሀብት ዘርፏል፣ አውድሟል። አሁንም ይሄንን እኩይ ድርጊቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

አሸባሪው ትህነግ ሚስትን ከባሏ ፊት፣ ልጅን ከአባቷ ፊት ደፍሯል። ከህፃን እስከ አዋቂ በጅምላ ጨፍጭፏል። ይህንን ጭፍጨፋ በአማራ ክልል ማለትም ማይካድራ፣ ጭና፣ ቦዛ፣ ቆቦ፣ አጋምሳ፣ ውጫሌ፣ ውርጌሳ እና በአፋር ክልል ጋሊኮማ ላይ ፈፅሟል።
አሸባሪው ትህነግ ብሔር እና ቦታ የማይወስናቸውን እና የሚሊዮኖች ሀብት የሆኑትን መንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ የሚከወንባቸውን አብያተ ክርስቲያናትን እና መስጂዶችን በምሽግነት ከመጠቀም ባለፈ አርክሷል፣ አውድሟቸውም ታይቷል። አገልጋዮችንም ረሽኗል።
የጨጨሆ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን አዲአርቃይ ወረዳ ዛሪማ ከተማ በሚገኘው መስጂድ ላይ በከባድ መሳሪያ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መረጃ እንደሚያሳየውም በሰሜን ወሎ፣ በዋግ ኽምራ፣ በደቡብ ወሎ አካባቢዎች በርካታ መስጂዶችና መድረሳዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ አማኞችም ተጎድተዋል።
አሸባሪው ትህነግ ካልተወገደ ነገም እነዚህን ውድመቶች ከመድገም ወደኋላ እንደማይል ግልፅ ነው። ግፍ ከመስራት፣ ሰቃይ ከማብዛት፣ ንጹኀንን ከማሰቃየት አይመለስም።
የትህነግ ሽንፈቶች
አሸባሪው እና ወራሪው ትህነግ የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል መውጣቱን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሐምሌ 5/2013 ዓ.ም ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ በመክፈት ነበር ዳግም ጦርነት ያካሔደው።
አሸባሪው ትህነግ በአፋር ክልል ወረራ ፈፅሞ ነበር። ጦርነቱም ሕዝባዊ ቅርፅን የያዘ እና በከባድ መሳሪያዎች የታገዘ ነበር። በወቅቱ የአሸባሪው ትህነግ መሪዎች አፋርን በሰፊው ለማውደም በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ጦርነቱ እንደገቡ በተደጋጋሚ በይፋ ተናግረዋል። ይሁን እንጅ ጀግናው የአፋር ሕዝብ ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በግንባር በመሠለፍ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ አድርጎ ወራሪውን ትህነግ ከክልሉ እንዲወጣ ማድረግ ችሏል። አሸባሪው ትህነግ ተዋርዶ እና በከፍተኛ ኪሳራ ተሸንፎ ከአፋር ክልል ለቆ ከወጣ በኋላም ተመልሶ ለመግባት ያደረጋቸውን ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሁሉ መክሸፋቸውን የአፋር ክልል መንግስት አሳውቋል። ይሔ ከወር በፊት በአሸባሪው ትህነግ ላይ የተፈፀመ ጀብድ ነው።
በተመሳሳይም በነሐሴ ወር አሸባሪ ኀይሉ ባሕር ዳርን እቆጣጠራለሁ በሚል ቀቢፀ ተስፋ በጋይንት መስመር በከባድ መሳሪያ የታገዘ እልህ አስጨራሽ ውጊያ አድርጎ የጋይንት ጀግኖች ከጀግናው የወገን ጦር ጋር ተባብረው በፈፀሙት የመልሶ ማጥቃት ውጊያ አሸባሪ ቡድኑ በከፍተኛ ውርደት ተሸንፎ ከአካባቢው እንዲርቅ ሆኗል። ባሕርዳርን የመቆጣጠር ህልሙም ቅዠት ሆኖ ቀርቷል።
በሰሜን ጎንደር በኩል ሠርጎ በመግባት ጎንደርን ለመቆጣጠር ዳባት ላይ እልህ አስጨራሽ ውጊያ ያደረገው አሸባሪው ትህነግ በጀግናው የወገን ጦር እና የጎንደር ጀግኖች ተቀጥቅጦ ተሸንፏል። ጎንደር ከተማን የመቆጣጠር ህልሙም መክኗል።
አሸባሪው ትህነግ በቆቦ ወረዳ 3 ቀበሌዎችን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ውጊያ አድርጓል። በራያ ቆቦ ጀግኖች ሽንፈትን አስተናግዶ ተመልሷል። እስካሁንም ነፃነታቸውን አስከብረው አሸባሪውን ቡድን እየተፋለሙት ይገኛሉ።
በድሬ ሮቃ ወረራ ለመፈፀም ተደጋጋሚ ውጊያ የከፈተው አሸባሪው ትህነግ በአርሶ አደሩ ጀነራል ሀሰን ከረሙና በሌሎች የመሠሉ ጀግኖች ሙት እና ቁስለኛ ሆኖ ተመትቷል።
በዋግኽምራ በሰሃላ ሰየምትና በሌሎችም አካባቢዎች አሸባሪው ቡድን በጀግናው የዋግ ሕዝብና የወገን ጦር ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል፤ እየደረሰበትም ይገኛል፡፡
በወልቃይትና አካባቢውም ተደጋጋሚ ጥቃት ቢሞክርም ወልቃይቴዎች ከጀግናው የወገን ጦር ጋር ተሠልፈው ትህነግን ድል አድርገው በነፃነት መኖራቸውን ቀጥለዋል። አሸባሪው ትህነግ በእነዚህና በሌሎችም ግንባሮች ከፍተኛ ኀይሉ ተደምስሶ ከነፍስ ወከፍ እስከ ቡድን እና ከባድ መሳሪያዎች እያስረከበ ነው። በወገን ጦር እና በአማራ ሕዝባዊ ኀይል ተቀጥቅጦ ከፍተኛ ሽንፈትን እያስተናገደ ይገኛል።
ይህ ተስፋ የቆረጠ ቡድን ሰርጎ በገባባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ሁሉ እየተቀበረ እና እየተዋረደ ይገኛል። አሸባሪ ቡድኑ በሕዝብ ማእበል የታገዘ ወረራን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሕዝብን ለማደናገር እየተፍጨረጨረ ይገኛል፡፡
አሁንም የወረራ አቅጣጫ ትኩረቱን ደሴ እና ኮምቦልቻ በማድረግ ተደጋጋሚ ውጊያዎችን እያደረገ ነው። ዛሬም አሸባሪው ትህነግ ደሴ እና ኮምቦልቻን ለመውረር እና ለመዝረፍ ያለ የሌለ ኀይሉን ሁሉ አሰባስቦ የሞት ሽረት ውጊያ እያደረገ ይገኛል። ይህንን ቡድን እነዚህን ከተሞች የመቆጣጠር ህልሙን ማክሸፍ፣ አዋርዶ እና አሸንፎ የድል ታሪክ መፃፍ የግድ ይላል።
በአፋር፣ በደባርቅ፣ በዋግ፣ በጋይንትና በሌሎች ግንባሮች የደረሰበትን የሽንፈት እና የውርደት ታሪኩን ዛሬም በወሎ ግንባሮች መድገም ይቻላል! አሸባሪውን ትህነግ ደሴ እና ኮምቦልቻን የመያዝ ህልሙን ቅዠት በማድረግ ከወረራቸው አካባቢዎች ቀብሮ ማስቀረት የሚቻልበት ወሳኙ ጊዜ አሁን ነው!
በሀብተጊዮርጊስ አበይ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ጠላት በወሎ ግንባር እያደረገ ያለውን ወረራ መግታት የሚቻለው ሕዝቡ ጠላትን መውጫና መግቢያ በማሳጣት፣ እርምጃ በመውሰድና እንደ ሕዝብ ወደ አካባቢው በመትመም ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀምበር
Next article“ኢትዮጵያ ትናንት ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለው ያሻገሯት ሀገር ናት፤ ዛሬም ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለን እናስቀጥላታለን” ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ማቴዎስ