”የአማራ ሕዝብ ነጻነቱን የሚያስከብረው በክንዱ ነው“ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ጀንበር

181

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕዝብ በጥንተ ጠላቱ ትህነግ ዛሬም የተለያዩ በደሎች እየደረሱበት ነው፡፤ ለዓመታት በኢትዮጵያ ስልጣነ መንበር ላይ የቆየው አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ስብስብ በአማራ ላይ እልፍ በደሎችን ፈጽሟል፤ ዛሬም መፈፀሙን ቀጥሏል፡፡ በመዋቅር የታገዘ በደል ሲፈጽም የነበረው አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ዛሬ ደግሞ ጦርነት ከፍቶ አማራን ወርሯል፣ ንጹኀንን ገድሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ ሀብት ዘርፏል፣ አውድሟል፤ አሁንም ግፎችን በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡

በወቅታዊ ጉዳይ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ጀንበር አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ በቃላት ሊገለጽ ከሚችል በላይ ግፍ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ አሁንም እየፈጸመ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የአማራ ሕዝብና መንግሥት ራሱን የማደራጀት ሥራ በመሥራት ጠላትን የመደምሰስ ሥራ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ በመደራጀት ባደረጋቸው አውደ ውጊያዎች ጀብዱዎች መፈጸማቸውን የተናገሩት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ጠላትን ከክልሉ ጠራርጎ ለማስወጣት አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ ነው ያመላከቱት፡፡

የጠላት ቡድን አሁንም በአማራ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ በደሎችን ለማድረስ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ጠላት ከቻለ አማራን አጥፍቶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማው አድርጎ እየሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የአማራ ሕዝብ በመደራጀትና በአንድነት በመንቀሳቀስ ጠላትን መቅበር ይገባዋልም ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ነጻነቱንና ፍትሕን ማግኘት የሚችለው ከማንም በስጦታ ወይም በልመና ሳይሆን በክንዱና በመስዋእትነት ነው፤ ይህም ተደራጅቶ በመውጣትና በመታገል ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ሁሉም ወደ ወሎ ይትመም የሚለው የክተት ጥሪ በተግባር እየታየ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ እድሜና ጤና የሚፈቅድላቸው የክልሉ ነዋሪዎችም ወደ ወሎና ወደ ሌሎች ግንባሮች እንዲዘምቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በቀረበው ጥሪ መሠረት ወደግንባር በመጉረፍ አማራ አንድነቱን ማሳየት አለበት፤ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ከዚህ በፊት እንዳደረገው ሁሉ ጠላትን እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ መንቀሳቀስ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የሰለጠኑ ወጣቶች ወደ ግንባር በመትመም ጠላትን መደምሰስ ይገባቸዋልም ነው ያሉት፡፡ ወጣቱ መከላከያን እና ልዩ ኀይልን እየተቀላቀለ ማጠናከር እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

ባለሀብቶችና ምሁራን በየድርሻቸው ወረራውን ቡድን ለመቀልበስ ተልእኳቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ጠላትን ማሸነፍ የሚቻለው፣ ደኅንነትን ማስከበር የሚቻለውና ሕልውናን ማስጠበቅ የሚቻለው በአንድነት ስንነሳ ነውም ብለዋል፡፡ ደጀን መሆን የሚገባው ደጀን በመሆን፣ መዝመት የሚችል በመዝመት የጠላትን ቅስም መስበርና ዳግም ወረራ እንዳይፈጽም ማድረግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ ሠራዊት ወደ ግንባር ሽኝት ተደረገለት፡፡
Next article“ጠላት በወሎ ግንባር እያደረገ ያለውን ወረራ መግታት የሚቻለው ሕዝቡ ጠላትን መውጫና መግቢያ በማሳጣት፣ እርምጃ በመውሰድና እንደ ሕዝብ ወደ አካባቢው በመትመም ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀምበር