በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እየተማሩ ነው፡፡

357
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ አማራ እና አማርኛ ቋንቋ ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ምድር እንዲጠፋ መዋቅራዊ ሰነድ በማዘጋጀት ታሪክ የማይረሳው ግፍ ፈጽሟል፡፡ በሽብርተኛው ትህነግ የግዞት ዘመን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተወለዱ ሕጻናት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆነውን አማርኛ በመናገራቸው ብቻ እንደ ወንጀል ሲቆጠርባቸው ቆይቷል፡፡ በትምህርት ቤትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብታቸውን ነፍጎ ለዓመታት ቆይቷል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው እንደ ማኅበረሰብ በአማርኛ ጭውውቶችን እና ዘፈኖችን ጭምር እንዳይተገብሩ ጫና ይደርስባቸው ነበር፡፡
የአማርኛ ሙዚቃ ለምን አዳመጣችሁ፣ የአማራ ባሕላዊ አለባበስ ለምን ለበሳችሁ፣ ለቅሶ፣ ሰርግ፣ ወዘተ ማኅበረሰቡ በራሱ ባሕል እና ቋንቋ ለምን አንጸባረቃችሁ ተብለው በርካቶች ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
አቶ ሙሉዓለም ገበየሁ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የወፍ አርግፍ ከተማ ነዋሪ ናቸው፤ በሽብርተኛው ትህነግ የሥልጣን ዘመን በማንኛውም ማኅበራዊ መስተጋብር አማርኛ ቋንቋን መጠቀም ሥርዓቱን እንደመቃወም ሌላውን እንደመደገፍ ተደርጎ ይቆጠር ነበር ብለዋል።
ሽብርተኛው ትህነግ የራሱን አጀንዳ ለማስፈጸም በቀረጸው ሕገ መንግሥት እንኳን ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር እንዳለባቸው ያስቀምጣል ያሉት አቶ ሙሉዓለም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አማራዎች ግን አሸባሪው ቡድን በኀይል ባስተዳደረበት ወቅት ማንነታቸው በማፈን የዚህ መብት ተጠቃሚ ሳይሆኑ ለዓመታት የሰቀቀን ኑሮ እንዲገፉ ተደርጓል ብለዋል።
አስተያየት ሰጪው እንደገለጹት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር ሲገባቸው በተቃራኒው ይህንን መሰረታዊ መብት ተነፍገው በማንነታቸው ሲሸማቀቁ በነበሩ ሕፃናት ላይ ደግሞ ተጽዕኖው ከባድ ነበር፡፡
በሽብርተኛው ትህነግ የሥልጣን ዘመን የነበሩ እነዚህ የሕዝብ መከራዎች ዛሬ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ምድር በተገኘው ነጻነት የማይደገሙ ነገር ግን የማይረሱ ግፎች ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት የአቶ ሙሉዓለም ገበየሁ ልጆችን ጨምሮ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪ ሕጻናት አፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሆነው አማርኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው። ይህም ለልጆቻቸውና ለእርሳቸው ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ነግረውናል። ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል፡፡ ሕዝቡም የተጎናጸፈውን ነጻነት ላለማስደፈር እና ዳግም ወደ ባርነት ላለመግባት ከመንግሥት ጎን በመሆን የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድንን መቅበር ግድ እንደሚል አቶ ሙሉዓለም ገልጸዋል።
ገብረጻዲቅ ሙሉዓለም የ6ተኛ ክፍል ተማሪ መሆኑን ነግሮናል፤ በሽብርተኛው ትህነግ የሥልጣን ዘመን በሚኖሩበት አካባቢም ሆነ በትምህርት ቤት አማርኛ መናገር እንደማይፈቀድላቸው አስታውሷል። በዚህም ከፍተኛ ሀዘን ሲሰማው እንደነበር ነው የገለጸው። አሁን ደግሞ በየትኛውም አካባቢ ሀሳባቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መግለጽ እንደሚችሉ ተናግሯል፤ ትምህርት ቤትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እየተማሩ ነው። ሂደቱም ከፍተኛ ደስታ እንደሰጠው ገልጿል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ገብረማሪያም መንግሥቴ እንደገለጹት ሽብርተኛው ትህነግ በኀይል ይዞት ከነበረው አካባቢ በእልህ አስጨራሽ ጦርነት ከተባረረበት ጊዜ ጀምሮ ነዋሪው የተለያዩ መብቶቹን በነጻነት መጠቀም ጀምሯል፤ ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል።
አካባቢው ከሽብርተኛው ትህነግ የግፍ አገዛዝ ነፃ ከወጣ በኋላ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት እየታየበት መሆኑን መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
በዞኑ በአሁኑ ወቅት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል 38 ሺህ 360 ተማሪዎች እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ 9 ሺህ 972 ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙም ኀላፊው አስረድተዋል። የትምህርት ዘርፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ግለሰቦች፣ ባለሃብቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ በፊት የሽብርተኛው ትህነግን ጫና በመቋቋም ወይም በስደት ላይ በመሆን ትምህርታቸውን የተከታተሉ የዞኑ ተወላጆች ለሀገርንና ለሕዝብን የላቀ አግልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
አሁን ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ደግሞ ሀገር ለመረከብ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ግብዓተ መሬት ተፈጽሞ የዞኑ ብሎም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ ደግሞ ሁሉም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኀይል፣ ከሚሊሻ እና ፋኖ ጎን በመሰለፍ በሕልውና ዘመቻው ታሪካዊ ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አቶ ገብረማሪያም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና ለችግር ለተዳረጉ ወገኖች 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ።
Next articleየባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ ሠራዊት ወደ ግንባር ሽኝት ተደረገለት፡፡