
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መግለጫ ሰጥተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጁታ ኧርፕላኔን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ የአውሮፓ ሕብረት የትህነግን የሽብር ድርጊት እንዲያወግዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጠይቀዋል፡፡
የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጁታ ኧርፕላኔን ኢትዮጵያ ስኬታማ ምርጫ ማከናወኗን በመጥቀስ ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልግ መግለጻቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል። ሕብረቱ ኢትዮጵያን በአየር ንብረት ለውጥ እና በሰው ኀይል ልማት ማገዝ እንደሚፈልግ ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል።
ኮሚሽነሯ ሁሉን አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ ያለምንም ችግር ለተጎጂዎች መድረስ እንዲችል መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንም ገልጸዋል፡፡
አቶ ደመቀ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጋርም ተወያይተዋል። በውይይቱም አሸባሪው ትህነግ በአፋር እና አማራ ሕዝቦች እየፈጸማቸው የሚገኙ ወንጀሎችን አብራርተውላቸዋል።
ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ