
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚመራው የወገን ጦር፣ በሕዝቡ ያልተቋረጠ ደጀንነት ሰሞኑን በኩታበር፣ ተሁለደሬ፣ ወረባቦና ጭፍራ ግንባር ፀረ ማጥቃት ርምጃ መውሰዱን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቃል።
በተመረጡ የጁንታው አሸባሪ ቡድን ማሠልጠኛዎች፣ የጦር ማደራጃና መገናኛ አውታሮች፣ የጸጥታ አካላት፣ አልባሳትና መሣሪያዎች ማምረቻ ላይ በንሥሩና በጀግናው የአየር ኃይል እንዳይነሡ ተደርገው መመታታቸውን ነው የገለጸው። በየግንባሩ በገፍ የሚያሰልፈው ኃይልም ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ ሆኗል ብሏል።
ጠላት የሚተማመንባቸው ከባድ መሣሪያዎቹ መክነዋል። በዚህም ምክንያት በጁንታው መንደር ጩኸትና ልቅሶ በርክቷል። የትሕነግ ሰሞነኛው ጩኸት የመተንፈሱ ምልክት እንደሆነ አስገንዝቧል። “የኢትዮጵያ መንግሥትን የተኩስ አቁምና ከትግራይ ክልል ጠቅልሎ የመውጣት ውሳኔን እንደ ሽንፈት ቆጥሮት ነበር፣ ለጋላቢዎቹ በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ እገባለሁ ብሎ ፎክሮ ነበር” ነው ያለው።
ሕልሙ ግን በጀግኖቹ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ተጋድሎ ወደ ቀን ቅዠት ተቀይሯል። በዚህም የተነሣ ጥቅምት 24 በግፍ ለጨፈጨፈው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሂሳብ አወራረድበታለሁ ላለው ሕዝብ ተማጽኖውን በማቅረብ ላይ ይገኛል። ሁኔታው የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይመርጡ ሆኖበታል ብሏል።
“በአንድ በኩል ጦርነቱ አብቅቷል መከላከያም እጁን ይስጥ ይላል። ይሄን ይረሳውና መፍትሔው ፖለቲካዊ በመሆኑ በሀገራዊ ምክክሩ አሳትፉን ይላል። የአሞሮች ጩኸት የሙታንን መብዛት የሚያሳይ ነው። መላው ሕዝባችን፤ አኩሪ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ያለው መላው የጸጥታ ኃይላችን ለአፍታም ቢሆን ግራ ለተጋባው ወራሪና ባንዳ የሽብር ቡድን ቅጥፈት ጆሮ አይሰጠውም። ለጦር ግንባር እንጂ ለወሬ ግንባር ቦታ የለውም። ሕዝቡም እየተነፈሰ ለሚጮኸው ጎማ ቁብ አልሰጠውም። ደጀንነቱና ኅብረቱን አጠናክሮታል። አሁን የሠራዊታችን ትኩረት በአቀባበሩ ላይ ነው። ሞቱ እንደማይቀር ተረጋግጧልና” ነው ያለው።
ወራሪውን መንጋ ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ቁልፉ መፍትሔ የተደራጀ የሕዝብ ንቅናቄ በመሆኑ መላው ሕዝቡ በተለይም ወጣቶች እያደረጋችሁ ያላችሁትን ተጋድሎ በማጠናከር የሕዝባችንን ህልውና፣ ክብርና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክን እንድትጽፉ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን አስታውቋል።
ለትግራይ ሕዝብ፤ እናትና አባቶች ለጥቂት ቅዠታሞች ብላችሁ የነገ ተስፋችሁ የሆነውን ተተኪ ትውልድ ለከንቱ ዓላማ እንዳትማግዱ፣ ቆም ብላችሁ በማስተዋል ለሀገራችሁ ጥብቅና እንድትቆሙ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረበ መሆኑን አስገንዝቧል። ጎማ በጣም ከጮኸ የመተንፈሱ ምልክት ነውና መላው የወገን ጥምር ጦርና ደጀኑ ሕዝብ ከብረት የጠነከረ ኅብረትንና ንቅናቄውን በማጠናከር፣ አሸባሪው ቡድንና መንጋው የገባበት ገብተህ በመቅጣት፣ ህልውናህን አስከብር! ውኃ የሚወስደው እሾህ ይጨብጣል። ጁንታው ያድነኛል ያለውን ሁሉ ለማድረግ መፍጨርጨሩ የሚጠበቅ እንጂ የሚያስደንቅ አይደለም ነው ያለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ