ጠላት ያለበት ድረስ በነቂስ ወጥቶ መደምሰስ ለነገ የሚባል ተግባር ባለመሆኑ በአንድነት ተሰልፎ መታገል ይገባል፡፡

188

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› እንደሚባለው የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሀገርን ለማፍረሥ ከጠመንጃ የበለጠ አቅም አለው፡፡ ፕሮፖጋንዳ አንድን ዓላማ ለማሳካት የሚውል መሳሪያ ነው፡፡ በዓለም ላይ ያለፉ መንግሥታትም የጠላታቸውን ዓላማ ለማክሸፍ እና ሕዝባቸውን ከጎናቸው ለማሰለፍ ተጠቅመውበታል፤ እየተጠቀሙበትም ይገኛል፡፡ ፋሽስቱ የጀርመኑ መሪ አዶልፍ ሂትለር ፕሮፖጋንዳን በስፋት ጥቅም ላይ ካዋሉት መሪዎች ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ አዶልፍ ሂትለር እ.አ.አ በ1933 በትረ ሥልጣኑን እንደተቆጣጠረ በፕሮፖጋንዲስትነቱ በሚታወቀው ጆሴፍ ጎብልስ የሚመራ የፕሮፖጋንዳ ተቋም በማቋቋም ‹‹ጠላቶቼ›› ባላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ አልሞ ሠርቷል፡፡

እ.አ.አ በ1935 ሂትለር ባወጣው ‹‹የኑረምበርግ ሕግ›› ላይም የጀርመን አይሁዶች ዜግነታቸውን እንዲነጠቁ አድርጓል፡፡ ‹‹የጀርመን ወይንም ተዛማጅ ደም አላቸው›› ተብለው ከሚታሰቡ ሰዎች ጋር ጋብቻም ኾነ ሌላ ግንኙነት እንዳይኖራቸው ከልክሏል፡፡ በዚህም ከ6 ሚሊየን በላይ አይሁዳውያን እና ጥቂት የማይባሉ ጂፕሲዎች በግፍ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ሌሎች ሀገራትን ለመውረር በተነሳበት ወቅትም ከሕዝቡ ድጋፍ ለማግኘት እንደ ትልቅ መሳሪያ ተጠቅሞበታል፡፡ በአጎራባች ሀገራት ላይ በዘራው የጥላቻ መርዝም ከዓለም ሀገራት ተገልሏል፡፡

አሸባሪው ትህነግም ገና ‹‹ሀ›› ብሎ ሀገር ለማፍረስ ጫካ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የሐሰት ፕሮፖጋንዳን እንደ ዋነኛ የመታገያ ስልት አድርጎ እየሠራበት ይገኛል፡፡

የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ያለውን ብዝኃነት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የበዳይ እና ተበዳይ ሐሰተኛ መረጃዎችን በመልቀቅ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሔርን ከብሔር ከዚያም አልፎ በአካባቢ ልዩነት በመፍጠር ህልውናውን ለማስጠበቅ ሠርቷል፡፡ በተለይም ደግሞ አማራ በሌሎች ሕዝቦች እንዲጠላ ሰፊ ሥራ ሠርቷል፡፡ ዓላማው ግቡን እንዲመታም የህቡዕ ቡድኖችን አቋቁሞ በሰፊው ሠርቶበታል፡፡ በዚህም የንጹሐን ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡

አሸባሪው ትህነግ አሁንም የተለመደውን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የማደናገር ሥራውን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የአማራ እና የአፋር ሕዝቦችን በመውረር ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል፡፡

የአማራ ጠላትነት ፍረጃ ሐሳቡ እና ተግባሩ ወደ ስልጣን እንደማያመጣው የተረዳው የሽብር ቡድኑ የአማራ ወኪል ናቸው ብሎ ያሰባቸውን የአማራ ምሁራንን በጠላትነት ፈርጆ መንቀሳቀስ ከጀመረ ዋል ብሎ አድሯል፡፡

በዚህ ወቅት ደግሞ የመከላከያን እና ሌሎች ተቋማትን ማኅበረሰቡ እንዳይተማመንባቸው ለማድረግ የተለመደ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሲያናፍስ እየተደመጠ ይገኛል፡፡ ይህም የሀገር መከላከያው ደጀን ሕዝብ እንዲያጣ በማድረግ ዓላማውን ለማሳካት ታልሞ የሚሠራ ነው፤ ይህንነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።

ሕዝቡ አሸባሪው ትህነግ በሚያሰራጨው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሳይደናገር አካባቢውን እየጠበቀ እና ለህልውናው አደጋ የሆነውን ጠላት ያለበት ድረስ በነቂስ ወጥቶ መደምሰስ ለነገ የሚባል ተግባር ባለመሆኑ በአንድነት ተሰልፎ መታገል ይገባዋል፡፡

አሁን ላይ ጠላት ኋላቀር በሆነ የጦርነት ስልት በሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሕዝብ ማዕበል ፈጥሮ ወሎን ለመውረር ያለ የሌለ አቅሙን አሰባስቦ እየተፍጨረጨረ ይገኛል፡፡ የአማራ ሕዝብም ይህን የሕዝብ ማዕበል ለመግታት የሚቻለው በሕዝብ ማዕበል መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹን አስተባብሮ ፊታውራሪ በመሆን ትኩረቱን ወደ ወሎ አድርጎ እና ሕዝባዊ ማዕበል ፈጥሮ ጠላትን ቀብሮ ወደ ልማት ሥራው መመለስ ይኖርበታል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleኑ ኢትዮጵያን በጠላቶቿ የማትበገር ሀገር እናድርግ- የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጥሪ
Next article❝ወራሪውንና ሽብርተኛውን ትህነግ ሳንቀብር ላንመለስ ተነስተናል❞ ከምዕራብ ጎጃም ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች ወደ ግንባር ያቀኑ የፖሊስ አባላት