
ጥቅምት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከአፍሪካ ሀገራት መካከል በነፃነት ቀንዲልነት ኢትዮጵያ ቀዳሚ ሆና ስትጠራ ነፃነቷ በልመና ወይም በችሮታ የተገኘ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ የምዕራባውያኑን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በመርህ ደረጃ እንኳን እንዳይነሳ አድርጋ የሰባበረችው በልጆቿ የተባበረ ክንድ ነው፡፡ ሞትን ንቀው የሀገራቸውን ነፃነት እና ክብር የሚያስቀድሙ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ጥንትም ነበሩ ዛሬም አሉ፡፡
ከውስጥ ባንዳ ከውጭ ጠላት አጥታ የማታውቀው ኢትዮጵያ ከማህጸኗ ጀግኖችም ነጥፈውባት አታውቅም፡፡ ደረታቸውን ለጦር እግራቸውን ለጠጠር ሰጥተው ሀገራቸውን ከጠላት የሚታደጉ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሆነው አልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ ነባሩ ለተተኪው አደራ እያለ ያቆያት ሀገር ናት፡፡ ዛሬ እና ነገም ፈተናዎቿ የማይከስሙት ኢትዮጵያ ነፃነቷ እና ሉዓላዊነቷ በልጆቿ ብርቱ ክንድ ብቻ የተረጋገጠ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ እና ተከብራ ትኖራለች” ለኢትዮጵያውያን ውርስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የገጠማትን ፈተና ተሻግራ ለመቀጠል ከትውልዱ ምን ይጠበቃል? ስንል በግንባር የሚገኙ የሠራዊቱን አባላት አነጋግረናል፡፡ በልጆቿ አጥንት እና ደም ታፍራ እና ተከብራ የኖረችውን ኢትዮጵያ ለማስቀጠል ወጣቱ መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
፲ አለቃ ፋሲካው ዘገየ ስለሀገሩ ክብር እና ስለሕዝቦቿ ደኅንነት ሲል ሁለት ጊዜ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መለዮን ለብሷል፡፡ የመጀመሪያውን የውትድርና ሕይዎት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደተቀላቀለ የሚናገረው ፲ አለቃ ፋሲካው ከሚወደው የውትድርና ሙያ እንዲገለል ያደረገው ብሔር ተኮር ብልሹ አሠራር ነበር፡፡ ፲ አለቃ ፋሲካው ሽብርተኛው ትህነግ በሥልጣን ዘመኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሀገር መከላከያን ማፍረስ ብሎ ሲተገብራቸው በነበሩ ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ አሠራሮች ከሚወደው ውትድርና ሙያ እንዲወጣ አደረጉት፡፡
የስድስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆነው እና በርካታ ሃብት እና ንብረት አፍርቶ ሕይዎትን በሌላ መንገድ የሚመራው ፲ አለቃ ፋሲካው ከ10 ዓመታት በኋላ ወደሚወደው የውትድርና ሙያ እንዲመለስ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን ሀገር እና ሕዝብን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ ወረራ መፈጸሙን ተከትሎ በታወጀው የክተት ጥሪ መከላከያን ተቀላቅሎ ሀገሩን በድጋሚ እያገለገለ ይገኛል፡፡
በወቅቱ የነበረው ቅሬታ በሽብርተኛው ትህነግ መራሹ ሥርዓት እንጂ በሀገሩ አለመሆኑን የተናገረው ፲ አለቃ ፋሲካው ሽብርተኛው ትህነግ ለኢትዮጵያ አደጋ መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው እንደሚገባ ገልጿል፡፡ ይህንን የሀገር ጠላት በመደምሰስ ኢትዮጵያን ከህልውና ስጋት ለመታደግ ሀገሩን እያገለገለ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የውትድርና ሙያን ከተቀላቀለ ዓመታትን እንዳስቆጠረ የነገረን ደግሞ ፲ አለቃ ቢኒያም ዳኘ ነው፡፡ “ሞት የትም፣ መቼም እና በማንም ላይ አለ” የሚለው ፲ አለቃ ቢኒያም ለሀገር ክብር እና ለሕዝቦቿ ደኅንነት ራስን መስዋእት ማድረግ ግን ልዩ ነው ይላል፡፡ እናም ሀገሩ በየጊዜው የሚያጋጥማትን ፈተና በጽናት እንድትሻገር ወጣቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡
“ከራስ በፊት ለሕዝብ እና ለሀገር” የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሚመራባቸው መሰረታዊ ቁልፍ ዕሴቶች አንዱ እንደሆነ የነገረን ፶ አለቃ ጥበበ መገርሳ ሀገር አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳው ሽብርተኛው ትህነግ እንደማይሳካለት ተናግሯል፡፡ ምክንያቱም አሁን ያልተሸራረፈ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የተላበሰ፣ ምንጊዜም የላቀ ጀግንነት ያለው እና በማንኛውም ግዳጅ የላቀ ውጤት የሚያስመዘግብ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እየተገነባ መምጣቱን ገልጿል፡፡
ከራስ በፊት ለሕዝብ እና ለሀገር የቆመ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መገንባት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ያለን ፶ አለቃ ጥበበ ይህንን መሰረታዊ ቁልፍ ዕሴት ለመተግበር ወጣቱ መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል አለበት ብሎናል፡፡ ፶ አለቃ ጥበበ ሕዝቡ ለሀገር መከላከያ ሠራዊቱ እያሳየ ያለው ፍቅር፣ ክብር እና ደጀንነት ተጨማሪ ጉልበት እየሆናቸው መሆኑንም ገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m