
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አባቶች መልካም ስምን ወድቆ የማይሰበር፣ ሞቶ የማይቀበር፣ አባት የሰጠ ወንበር ይሉታል፣ መልካም ስም ሞቶ አይቀበርም፣ ወድቆ አይሰበርም እና፡፡ መልካም ሰም በመቃብር አፈር አይረሳም፣ በዘመን ብዛት ክብሩ አይሳሳም፣ ከፍ እንዳለ ይኖራል እንጂ፡፡ ብልሀተኞች፣ ጀግኖችና ሩቅ አሳቢዎች በምድር በተሰጠቻቸው አላፊ እድሜ የማያልፍ ነገር ተክለው ይሄዳሉ፣ ስማቸውን እንደተራራ ያቆማሉ፣ እንደ ዘላለማዊ ወንዝ ያፈስሳሉ፣ እንደ ውቅያኖስ ያሰፋሉ፡፡ የስም ሞትን አብዝተው ይፈራሉ፣ የስጋ ሞት ለማንም አይቀርም፣ እርሱን ማሸነፍ አይቻልም፣ የማይሞት ስም ተክሎ ማለፍ ግን ይቻላል፡፡ ታላቅነትና ጀግንነትም ነው፡፡
ወዳጄ ጥቅምት ነውና ጥቅምት እኩሌታን አስብ፣ በትዝታ ወደዚያ ዘመን ሽምጥ ጋልብ፣ እምዬ ምኒልክ ሀገር ተወረረ፣ ሕዝብ ተደፈረ ብለው ያስነገሩትን አዋጅ ልብ በል፡፡ የዚያ ዘመን ኢትዮጵያዊያን በአንድ አዋጅ እንዴት እንደተሰባሰቡ፣ በአንድነት እንዴት እንደተመሙ፣ በሠንደቁ ግርጌ እንዴት እንደተማማሉ አስተውል፡፡ የምኒልክ ነጋሪት ሲያገሳ መላው ኢትዮጵያዊ ነው በአንድነት የተነሳ፡፡ ነጋሪቱ ሲጣራ የሀገሬው ሰው ከተቀመጠበት ተነሳ፣ ነፍጡን ከራስጌው አነሳ፣ አሳምሮ ወለወለ፣ ጎራዴውን ሳለ፣ ትጥቁን አስተካከለ፣ ፈረስ ያለው ፈረሱን ጫነ፣ ፈረስ የሌለው በእግሩ ለመዝመት ቆረጠ፡፡ ነብሱን ሰጥቶ ሊያስከብራት፣ እርሱ ሞቶ ሊያኖራት፣ በክንዱ ጠላትን ሊቀጣላት አሻፈረኝ ብሎ ተነሳ፡፡
በጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ላይ ከትተኽ ጠብቀኝ ያሉት አባ ዳኛውና ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ታጅበው ከቤተመንግሥታቸው ሲነሱ አባቶች መረቋቸው፣ እናቶች በድል ይመለሱ ዘንድ አብዝተው ለመኑላቸው፣ ጎልማሶች እየሸለሉና እየፎከሩ ተከተሏቸው፣ የጦር አበጋዞቻቸው በፊት፣ በኋላ፣ በግራ በቀኝ ከበቧቸው፣ የእውነት፣ ለእውነት፣ በእውነት የተነሱት ንጉሡ የሚያምኑት ፈጣሪያቸው አሳፍሮ እንደማይመልሳቸው ልባቸው አምኗል፡፡ ለግፍ ዘመቱ እንጂ በግፍ አልዘመቱምና ፈጣሪ ከግፉዋን ጋር እንደሚሆን አልተጠራጠሩም፡፡
ጥርጣሬ ያልተገኘበት እምነት፣ ጉድፍ ያልተገኘበት ጀግንነት ሰንቀው ተነሱ፡፡ ትቢት የወጠረው የጣልያን ጦር በሰሜን ኢትዮጵያ የተከበረችውን ምድር ረግጧል፡፡ ከልክ አልፏል፣ የተዳፈነውን እሳት ቆስቁሷል፣ የተኛውን አንበሳ ቀስቅሷል፣ ነብሩን አስቆጥቷል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በንጉሣቸው ጥሪ መሠረት፣ ለሠንደቃቸው ክብር፣ ለሀገራቸው ፍቅር ሊዋደቁ ከንጉሣቸው አስቀድመው ወረኢሉ ለመድረስ ወደ ሥፍራው ተመሙ፡፡ ሀገሩ ጉድ አለ፤ ʺሀገሬን ጠላት ከሚደፍርብኝ ከድንበሯ ላይ መሞት አለብኝ” እያሉ ወደፊት ገሰገሱ፡፡
ኢትዮጵያን የማያውቋት የውጭ ነገሥታት ወዮላት ለዚያች ሀገር አሉ፡፡ ከሮም የተነሳው ጦር የሮምን አደባባዮች አጨናንቋቸዋል፣ ፎክሮባቸዋል፣ ዝቶባቸዋልና ያን የሠለጠነ ሠራዊት ማን ያስቆመዋል ተባለ፡፡ ወዮላት ኢትዮጵያ የሚላት በዛ፡፡ ኢትዮጵያዊያንም ሙያ በልብ ነው ብለው የልባቸውን መሻት ሊፈጽሙ ጠላት ወደመጣበት፣ ሞት ወዳለበት ሥፍራ ተፋጠኑ፡፡ ተስፋ ለቆረጡት ተስፋ የሆነች፣ ከተመረጡት የተመረጠች፣ ከተከበሩት የተከበረች፣ ከጉልበተኞች ሁሉ በላይ የሆነች፣ መልካሙን ዘመን ያመጣች፣ የጭቆናውን ዘመን የፈጸመች፣ የሰውን ዘር እኩል ያደረገች፣ ጠላትን በሚገባ የቀጣች፣ ኀያላኑን ያስደነገጠች ታላቋ ኢትዮጵያ ማን ሊደፍራት፣ ማንስ ሊነካት፡፡ በምኒልክ አዋጅ የተሰባሰቡት፣ በአንዲት ኢትዮጵያ የተማማሉት፣ ለእናት ሀገራቸው ነብሳቸውን ለመስጠት የቆረጡት ጀግኖች ወረኢሉ ላይ ተገናኙ፡፡
ንጉሡም በታላቅ አጀብ ሲገሰግሱ ደረሱ፤ መነሻውም መዳረሻውም ሀገርን ማዳን ነውና ምክር ተደርጎ ጉዞ ጠላት ወደ አለበት ሆነ፡፡ በአምባላጌና በመቀሌ ምሽግ የሠራውን ጠላት ድባቅ መትተው ወደ ፊት ገሰገሱ፣ የመጨረሻው የድል ማብሠሪያ፣ የአፍሪካዊያን ጮራ መዝለቂያ፣ የቀኝ ገዢዎች ዘመን ማብቂያ የሚበሰርበት ተራራ አጠገብ ደረሱ፡፡ ወደ ተራራው ጫፍ ገሰገሱ፤ የማይቀረው ፍልሚያ ተጀመረ፣ ለዓመታት ይዋጋል፣ ኢትዮጵያን ያጥለቀልቃል፣ ለሮም ነገሥታት፣ መሳፍንትና መኳንንት፣ ወይዛዝርትና ጎበዛዝት ሁሉ የድል ብሥራት ያደርሳል የተባለው ሠራዊት ከግማሽ ቀን በላይ መቆዬት አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ አፈር በላው፣ የጀግኖች ጎራዴ ቀላው፣ ሳንጃቸው ወጋው፣ ጦራቸው ሰቅዞ ያዘው፤ ያ ሁሉ የጠላት ጦር እንዳልነበር ሆነ፡፡ የእኩልነት ጀንበር በዓድዋ አናት ላይ በራች፡፡ በሮም ምድር ላይ ብርሃኗን ከለከለች፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ በደስታ ተፍለቀለቀች፡፡ የድል ብሥራት የጠበቁት የሮም ነገሥታት ውርደት ደረሳቸው፣ ሀዘን ሰበራቸው፣ ጨለማ ዋጣቸው፣ ሀፍረት አሰራቸው፣ የድል ዜና ለመስማት የቋመጠው ዓለም ሁሉ ደነገጠ፣ ማዕበል እንደመታው ባሕር ተናወጠ፡፡
ʺሳይደርሱባቸው እየደረሱ፤
ይመለሳሉ እየቀመሱ” እንዲሉ ሳይደርሱባቸው የደረሱት ሁሉ ቀምሰው ተመለሱ፣ ልጇን ኢትዮጵያዊያንን ውጋ ብላ የላከች የጣልያን እናት ያችን ቀን ረገመች፣ አብዝታ አዘነች፣ አፈረችም፡፡ ሂድ ጀግናዬ ሀገርህን አስከብር፣ ዝመት፣ መክት ያለችው የኢትዮጵያ እናት ደግሞ አበጀሁ ጀግና ወልጃለሁ ስትል ኮራች፣ በደስታ ተመላለሰች፣ በአሸናፊነት ደመቀች፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በሚለው መጻሕፋቸው ʺ ከዓድዋ ጦርነት ወዲህ የኢትዮጵያ ስም ፀሐይ ባየው ሀገር ሁሉ ታወቀ፡፡ ከዚያ በፊት ኢትዮጵያ ምንም ከጥንት ከመሠረት ጀምራ ራሷን ችላ ብትኖር ከቶውንም በነፈርኦን ጊዜ ተባሕር ወዲያ እስከ ምስር ባንድ፣ ባንድ ወገንም እስከ አደን ካረብ ሀገር ተሻግራ ብትገዛም በአውሮፓውያን ስሟ የአሕዛብ ሀገር ናት ትባል ነበር፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ኀይል፣ በዳግማዊ ምኒልክ እውቀት ዛሬ ግን ኢትዮጵያ እውነተኛ ስሟ ተገለጠ፡፡ ከእውነተኛ ማዕረጓ ገባች” ሲሉ አስፍረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ትክክለኛ ማዕረጓ ማሸነፍ፣ ከፍ ከፍ ማለት ነው፡፡ ዛሬም እንደ ጥንቱ ሀገርህ ላይ ጠላት ተነስቷል፡፡ ምኒልክ በጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ከትተህ ላግኝህ እንዳሉ ሁሉ ዛሬም ሁሉም ወደ ወሎ ይትመም፣ ይዘመት ተብሏል፡፡ የዛን ጊዜው ነጋሪት ተመትቷል፣ የዛን ጊዜው አዋጅ ተነግሯል፣ ጠላት ወገን ገድሏል፣ ገፍቷል፣ አሰቃይቷል፡፡ ዓይኖች ሁሉ ወደ ወሎ ይዩ፣ እግሮች ሁሉ ወደ ወሎ ይጓዙ፤ ልቦች ሁሉ ስለ ወሎ ያስቡ፣ በወሎ የገባውን ጠላት ለማስቀረት፣ ኢትዮጵያን ለማጽናት ሁሉም ወደ ወሎ ይዝመት፡፡ ጠላት ሀገርህን ሲወር፣ ወንዝህ ሲደፈር ማዬት እንደምን ይቻላል? የምኒልክ ቃል የተተገበረበት፣ ጀግኖች የተሰባሰቡበት፣ ወደ ከፍታ ለመሄድ የመከሩበት፣ ጠላትን አንገት ያስደፉበት ምድር ወሎ ተወሮ ችሎ የሚቀመጥ የለም፡፡ ወደዚያው ዘምቶ፣ ጠላትን በዚያው አስቀርቶ ወገንን ነጻ አውጥቶ፣ የሰላም ጮራ አውጥቶ መመለስ ነው እንጂ፡፡ የንጉሥ ሚካኤልን ሀገር ጠላት አይደፍረውም፣ ሀዘን አይገባውም፣ ዘራፍ ብሎ ተነስቶ፣ ጠላትን ድባቅ መትቶ ቀዬውን ማስከበር፣ አድባሩን ማክበር ነው እንጂ፡፡ የእምዬ ምኒልክን አደራ ጠብቅ፣ የሀገርህን ፍቅር አጥብቅ፤ እምዬ ምኒልክ ʺ … ነፋስ እንዳይገባባችሁ ሀገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ ወንድሜ፣ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፣ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ከደንበር መልሱ፡፡ የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንዱ ወገን ቢሄድና ደንበር ቢጋፋ በኔ ወገን ካልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፡፡ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ሄዳችሁ በአንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ በየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ፡፡ ይህንን ምክር ለእናንተ መስጠቴ እኔማ በእግዚአብሔር ቸርነት ይህንን ያክል ዘመን ገዝቸ የለምን ? … ተስማምታችሁ የኢትዮጵያ ደንበር እንዲሰፋ እንጂ አንድም ጋት መሬት እንዳይጠብ አድርጉ፣ ጠብቁ፣ አልሙ፡፡ የደጊቱ የሀገራችን የኢትዮጵያ አምላክ ይገዛችሁ፣ ይጠብቃችሁ፡፡ ከዚህ ቃል የወጣ በሰማይም ነፍሱ በምድርም ስጋው እስከ ልጅ ልጁ የተረገመ ይሁን የኢትዮጵያ ውቃቤ ያጥፋው፡፡” ሲሉ ታላቅ ቃል አኑረዋል፡፡
እነሆ ጠላት ዛሬ ሀገርህን ወሯል፣ ወገንህን አሰቃይቷልና እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነህ ተነስ ዝመት፣ ክተት፣ መክት፡፡ ቀልብህን፣ ልብህን፣ ዓይንህን፣ እግርህን፣ ክንድህን ሁሉንም ነገር ወደ ወሎ አዙር፣ በደጋጎች ቀየ የገባውን አድባር ሊያረክስ የመጣውን በዚያው አስቀር፣ መቃብሩን በጥልቀት ምሰህ ቅበር፡፡ ይህን ሳታደርግ ብትቀር ግን ቃል ትበላለህ፣ መሃላ ታፈርሳለህ፣ ታሪክ ታጎድላለህ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m