
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አባቶቻችን በጦርና በጎራዴ ተዋግተዉ ያቆዩልንን ሀገር አናስደፍርም ያሉ የአማራ ሳይንት ወረዳ ጀግኖች ወደ ግንባር አቅንተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ማፍረስ ዓላማው አድርጎ ወረራ የፈጸመው ሽብርተኛው ትህነግ ወረራ በፈጸመባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች እየፈጸመ ያለው ግፍ ያንገሸገሻቸው ሁሉ በቃ በሚል ስሜት ሆ ብለው ተነስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሀገሩ ቀልድ የማያውቀው ኢትዮጵያዊ ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ወሎ እየዘመተ ነው፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ የማይደፈር ደፍሯል፤ የማይነካ ነክቷል፤ ግብብተ መሬቱን ሳይፈጸም ላይመለስ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተማምሎ ወደ ወሎ ክተት ተጠራርቷል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን አማራ ሳይንት ወረዳ ነዋሪዎች በነቂስ ወደ ግንባር እየተመሙ ነው፡፡ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ግፍ ወደ እያንዳንዱ ቤት እየመጣ ነውና እዛው ቀብሩን መፈጸም ግድ እንደሚል ነው ጀግኖቹ የገለጹት፡፡ እናም ክተት ወደ ወሎ ብለዋል፡፡
ከዘማቾቹ መካከል አቶ አበበ ጌታነህ “እኔ ከታሪካችን እንደማውቀው አባቶቻችን በባዶ እግራቸው በገደል ጢሻውን እየጣሱ ያላቸውን ስንቅ በመሸከም በውጅግራ፣ በጎራዴ፣ በዲሞፍተር እየተዋጉ ሀገራችንን አቆይተዋል” ሲሉ ሀገር ተደፍራ የማየት ሞራል እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ እናም ሽብርተኛው እና ከሀዲው ትህነግ ኢትዮጵያን ሲያፈርስ፣ ሕዝቧን ሲገድል፣ ሲያጎሳቁል ዝም ብለው ማየት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
አቶ አበበ ሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ለማንም የማይራራ ግፈኛ በመሆኑ ወሎ ምድር ላይ ቀብሩን ለመፈጸም ሁሉም እንዲተም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እዛው እንገናኝ ብለው እሳቸው ጉዞ ጀምረዋል፡፡
ሌላው ዘማች አቶ ሰጡ ብርሃኔ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን የሚፈጽመው ግፍና መከራ በቃ ሊባል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ እናም ደጃቸው እስኪመጣ ባለመጠበቅ እዛው ድረስ ሄደው የኢትዮጵያ ጀግኖችን ብርቱ ክንድ ሊያሳዩት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አማራ ሳይንቶች “ኑ ወሎ እንገናኝ” ብለው ወደ ግንባር አቅንተዋል፡፡ መረጃው የአማራ ሳይንት ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ