❝አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ እስኪቀበር ድጋፋችን እንቀጥላለን❞ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

180
ደሴ: ጥቅምት 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ ነዋሪዎች በእውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ስለሕዝብ ሰላም የገቡትን ህያው ቃል አፅንተው በዱር በገደሉ ከጠላት ጋር ለሚዋደቀው የወገን ጦር ማዕድ አጋርተዋል።
በደሴ ከተማ አስተዳደር ሆጤ ክፍለ ከተማ በሀገር ግዛት ቀበሌ የሚገኙ 12 እድሮች የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር ነው ማዕድ ያጋሩት።
የማዕድ ማጋራቱን ካስተባበሩት መካከል አቶ ዘሪሁን ማንደፍሬ ❝ለሀገርና ደኅንነትና ለሕዝብ ሰላም በጦር ግንባር ተሰልፎ እየተዋደቀ ላለው የወገን ጦር የተቀናጀ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያስፈልጋል❞ ብለዋል።
የወገን ጦር የአሸባሪውን የትህነግ አከርካሪ ሰብሮ በወሎ ምድር እንዲቀበር የሚያደርገውን ትግል በማገዝ ትኩስ ምግብ አዘጋጅተው ማዕድ እንዳጋሩ ነው የገለጹት።
በግንባር የተሰለፉ የመከላከያ፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ በአሸባሪውና ወራሪው ትህነግ የተከፈተብንን ጦርነት በአሸናፊነት ደምድመው ለሕዝባችን የድል ብስራትን እስኪያሰሙ ድረስ የኅብረተሰቡ ድጋፍ እንደሚቀጥልም አቶ ዘሪሁን አስረድተዋል።
❝አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ እስኪቀበር ድጋፋችን እንቀጥላለን❞ ነው ያሉት።
ስለ ሀገርና ሕዝብ ብሎ በጦር ግንባር ህይወቱን እየከፈለ ላለው የወገን ጦር የደሴ ከተማ ሕዝብ የሚሰስተው ነገር የለም ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ አሕመድ ሙሐመድ ናቸው።
ለወገን ጦር ያላቸውን ኹሉ በማድረግ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
በግንባር ለተሰለፈው የመከላከያ፣ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ከሚያደርጉት የምግብ ድጋፍ በተጨማሪ በአሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖችም ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም አቶ አሕመድ አስረድተዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ሰብለ አበባው በበኩሏ አሸባሪው ትህነግ በወሎ ምድር እንዲቀበር ሴቶች ጠንካራ ደጀን ኾነው መቀጠላቸውን ገልጻለች።
ያደረጉትን የማዕድ ማጋራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግራለች። በቀጣይም ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችን ለወገን ጦር እንደሚያደርጉም አስረድታለች።
ዘጋቢ:- ግርማ ሙሉጌታ – ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ለእናት ሀገሬ አይደለም መዝፈን ግንባር ድረስ በመዝመት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ❞ ድምጻዊ መስፍን በቀለ
Next article❝የሽብርተኛው ህወሓት የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሠራዊታችንን የድል ግስጋሴ አይገታውም !❞ መከላከያ ሠራዊት