“አሸባሪው ትህነግ በወሎ ይቀበራል” ያሉ የአዲስ አበባ ወጣቶች ወደ ወሎ ዘመቱ።

806

ደሴ፡ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) ያስተላለፉትን “ሁሉም ወደ ወሎ ይዝመት” የክተት ጥሪ የተቀበሉ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ወደ ወሎ ዘምተዋል፡፡ ወጣቶቹ “አሸባሪው ትህነግ በወሎ ይቀበራል” በሚል ወኔ ወደ ወሎ ግንባር መዝመታቸውን ነው ለአሚኮ የተናገሩት።

ይልማ ሙሉጌታ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆን የከተማዋን ወጣቶች በማስተባበር በወሎ ግንባር ተሰልፈው ጠላትን ቀብሮ ለማስቀረት ደሴ ከተማ እንደተገኙ ተናግሯል። የወሎ ወጣት ለዓመታት በአሽባሪው ትህነግ የግፍ በትር እንደደረሰበት የገለጸው ወጣት ይልማ አሁን ላይ የወሎ ወጣቶች አሸባሪው ትህነግን በወሎ ምድር ቀብረው አንገታቸውን በኩራት ቀና አድርገው የሚኖሩበት ጊዜ መቃረቡን ተናግሯል።

የደሴና የአካባቢው ወጣቶች አሸባሪው ትህነግን በወሎ ምድር ቀብሮ ለማስቀረት ከፍተኛ ወኔ እንዳላቸው መመልከቱን የሚገልጸው ወጣት ይልማ “እኛም ከአዲስ አበባ የመጣነው ወጣቶችን በማገዝ በወሎ ግንባር ለተሰለፉ የጸጥታ አካላት ተጨማሪ ኀይል ለመሆን ነው” ብሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ኡስማን መሐመድ በበኩሉ ሀገር ከሌለ ሰርቶ መለወጥ አይቻልም ለዚህም ነው መዝመት የሚያስፈልገው ነው ያለው። “እኛ በወሎ ግንባር የተገኘነው የሀገር ጠላት የሆነውን ትህነግ እዚሁ ወሎ ምድር ላይ ቀብረን ሀገራችንን በማስቀጠል ህልውናችንን ለማረጋገጥ ነው” ሲልም ያስረዳል።

በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች በሀሰት ወሬ ሳይፈቱ ወደ ወሎ ግንባር በመዝመት ጠላትን በወሎ ምድር ላይ ለመቅበር በሚደረገው ትግል ታሪካዊ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ወጣት ኡስማን ጥሪ አቅርቧል።

ሌላው ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ ግንባር በመዝመት ወጣቱን እያስተባበረ የሚገኘው ወጣት ሳልህ አብዱል የአማራ ክልል መንግሥት “ሁሉም ወደ ወሎ ይዝመት” ማለቱን ተከትሎ ወደ ግንባር መንቀሳቀሱን ይገልፃል። “የወራሪውን የመጨረሻ መቀበሪያ ወሎ ምድር ለማድረግ ከሚያቀርቡት የሎጂስቲክስ ድጋፍ በተጨማሪ ወጣቱን አስተባብረው ወደ ግንባር በመሄድ ከአሸባሪው ጋር ፊት ለፊት ለሚፋለመው ኀይል ተጨማሪ ጉልበት ለመሆን ግንባር መገኘታቸውን አስረድቷል።

ዘጋቢ:- ግርማ ሙሉጌታ-ከደሴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“በእኛ የሕይወት መስዋእትነት የነገው ትውልድ በነጻነት እንዲኖር እንዋደቃለን” የምሥራቅ አማራ የፋኖ አባላት
Next article❝የወገን ጥምር ጦር የፀረ ማጥቃት ርምጃ፣ ወራሪውን መንጋ መውጫ መግቢያ እያሳጣው ነው❞ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት