
ደሴ፡ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ አማራ የፋኖ አባላት ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት የአሸባሪው ትህነግን ወራሪ ቡድን ወሎ ላይ ቀብሩን ለመፈጸም እየተፋለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ፋኖ ፈቃድ አበበ በአማራ ላይ እየደረሰ ያለው መከራና ግፍ እንዲያበቃ ውድ ሕይወቱን ለመስጠት ግንባር ተሰልፏል፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ በሠራው ግፍ እናቶች በጫካ ሲወልዱ፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አዛውንቶች በባዶ ቤት እንዲዘጉ ከማድረግ በላይ ግፍ የለም ሲል ተናግሯል፡፡ ይህ ግፍ የሚያበቃው በእኛ መስዋእትነት ነው የሚለው ፋኖ ፈቃድ የሰው ልጅ የሚሳሳለትን ሕይወት ለመስጠት ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ ጀብዱ እየፈጸሙ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡
ፋኖ ፈቃድ “የእኔ መስዋእት መሆን ነገ ሕጻናት በነጻነት እንዲያድጉ ያደርጋል” ብሏል፡፡
ፋኖ መምህር ሲልአምላክ ደጉ ወገንን ሽብርተኛው ትህነግ ከሚያደርስበት ስቃይ ለመታደግ የሚወደውን የመምህርነት ሙያ ትቶ ፋኖን ተቀላቅሎ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ ጠመኔውን ትቶ ፋኖን የተቀላቀለው ሲልአምላክ ከጠላት ጋር ተናንቆ የጦር መሳሪያ እንደታጠቀም ነግሮናል፡፡ “ያለ መስዋእትነት ነጻነት የለም” ሲል የሚገልጸው ፋኖ ሲልአምላክ ሁለት ጊዜ ቆስሎ አገግሞ አሁንም በአውደ ውጊያ እየተሳፈ ይገኛል፡፡ “በእኛ የሕይወት መስዋእትነት የነገው ትውልድ በነጻነት እንዲኖር እንዋደቃለን” ብሏል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ፋኖ ድረስ ብርሃኔም “ወገኔን ከሽብርተኛው ትህነግ ግፍ ታድጌ በጀግንነት ስፋለም ብሰዋ ክብርና ኩራት ይሰማኛል” ነው ያለው፡፡ በትግል ሂደት ውስጥ ቢያልፉም ታሪክ ጀግንነታቸውን እንደቀደሙት ሁሉ ሲዘክረው እንደሚኖርም ገልጿል፡፡
ፋኖዎቹ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ተገቢውን ቅጣት እየቀጡት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኀይል፣ ከሚሊሻና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙም ፋኖዎቹ ገልፀዋል፡፡
የፋኖ አባላቱ ወጣቶች ከአሉባልታ ወጥተው የደጀንነት ሥራቸውን አጠናክሮ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የደቡብ ወሎና የደሴ ከተማ ወጣቶችና ማኅበረሰቡ እያደረጉ ያለው መልካም ሥራ እውቅና ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m