
ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/2012 ዓ/ም (አብመድ) የበርካታ ነዋሪዎች ሕይወት ከጣና ሐይቅ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው፡፡ ጣና ሐይቅ ለባሕር ዳር ሳንባዋ ነው፤ ውበቷም ነው፤ ለበርካቶች የኢኮኖሚ ምንጭም ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የግለሰቦች ጥንቃቄ የጎደለው ዕለታዊ እንቅስቃሴ ለሐይቁ ኅልውና ስጋት እየሆነ ነው፡፡ የፕላስቲክ ውጤቶች በሐይቁ ውስጥና ዳርቻ ተጥለው ማየት የተለመደ እየሆነም መጥቷል፡፡ ያነጋገርናቸው ግለሰቦች የፕላስቲክ ውጤቶች በአብዛኛው በሐይቁ ዳርቻ ለመዝናናት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ሰዎች የሚጥሏቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቀሪዎቹ ደግሞ ኃላፊነት በማይሰማቸው ጎብኝዎች የተጣሉ ናቸው፡፡
አንዳንድ ግለሰቦች በሐይቁ ውስጥ ልብሳቸውን ሲያጥቡ፣ ሰውነታቸውንም ሲታጠቡ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህን ተከትሎ ለጽዳት የሚጠቀሙበት እንደ ኦሞ፣ ሳሙና፣ በረኪናና መሰል ማጽጃ ኬሚካሎች በብዝኃ ሕይወቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ድርጊቱ የሐይቁን መልካም ተፈጥሯዊ ገፅታ መመልከት ለሚፈልጉ ምቾት የሚሰጥ አለመሆኑን ያነጋገርናቸው ጎብኝዎች ትዝብታቸውን ነግረውናል፡፡
ጉዳዩ የሚመለከተው የአማራ ክልል የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን በሐይቁ ላይ እየተስተዋሉ የሚገኙ ሰው ሰራሽ ችግሮች ማኅበራዊ ኃላፊነትን በትክክል ባለመወጣት የሚከሰቱ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ማኅበረሰቡ ሐይቁን እንዴት መንከባከብ እንዳለበትና ፕላስቲክ እና መሰል ቀሻሻ ወደ ሐይቁ እንዳይጣል ግንዛቤ እየፈጠረ መሆኑን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡
አስጎብኝዎችንና በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር በየወሩ የጽዳት ሥራ መጀመሩንም የባለስልጣኑ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ይታይ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሐይቁን እየበከሉ ያሉ ፕላስቲክ ቆሻሻዎች መልሰው ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግም በዘርፉ ልምድ አላቸው ከተባሉ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት መታቀዱም ተብራርቷል፡፡ ከአንድ የጀርመን ድርጅት ጋርም በቅንጅት ለመሥራት ምክክር እየተደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ጽዳትና ውበት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ጌታሁን ደግሞ ሐይቁ የገላ መታጠብን ለመቀነስ በበጀት ዓመቱ ሦስት የሕዝብ መታጠቢያ ቤቶች እንደሚገኙም ነው የተገለጸው፡፡ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሦስት ቋሚ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች በሐይቁ አካባቢ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ተጨማሪ መጸዳጃ ቤቶችና የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን በጣና ሐይቅ ዳርቻ ለመገንባት ከአጋር አካላት ጋር እየተሠራ ነውም ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ