
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዋጋ ንረት የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር እና ሩዝ ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑን ነሐሴ 28/2013 ዓ.ም ነበር የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወሳኝ በሆኑ ሸቀጦች ላይ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያ መደረጉም ይፋ አደርጎ ነበር። ፖስታ እና ማካሮኒ የጉምሩክ ቀረጡ እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንደተነሳላቸው ነው የተወሰነው፡፡ ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር እና የሩዝ ምርቶች ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ግዥ ሲፈጸም ከማንኛውም ቀረጥ ነጻ እንዲሆኑ ተወስኗል። ከዚህ ባለፈም በዶሮ እንቁላል ላይ የነበረው ተጨማሪ እሴት ታክስ ፍላጎት እና አቅርቦት እስከሚጣጣም ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ ሆኖ ለገበያ እንዲቀርብ ተወስኗል።
ይህ የመንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያ በገበያ ላይ የዋጋ ማሻሻያ አምጥቶ በኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ለውጥ ታይቷል የሚባለው አሁንም አጠያያቂ መሆኑን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው ሸማቾች ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ወሰኔ ገሰሰ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የቀበሌ 13 ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ መንግሥት ስኳርን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎችን ከቀረጥ እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀኖች ሰምተዋል፡፡ ነጻ እንዲገቡ የተወሰነላቸው መሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች በጥቂት ቀናት ውስጥ ዋጋቸው እንደሚቀንስ እና በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት እንደሚችሉ ጠብቀው እንደነበር ነግረውናል፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ ገበያ ላይ ያገኙት ዋጋ ግን የማይታመን ነው፡፡ 5 ሊትር ፈሳሽ ዘይት ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት 545 እየተሸጠ ነው ብለዋል፡፡ ሌሎች ሸቀጦችም የታሰበውን ያህል ዋጋቸው አለመቀነሱን ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ የዋጋ ጭማሪ ሲፈጠር የመጠየቅ ልምድ ቢኖራቸውም የሚሠጣቸው ምላሽ ተመሳሳይ እና መፍትሔ የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በገበያው ጣልቃ ገብቶ እንዲያስተካክለው ጠይቀዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዋ እንደተናገሩት ማኅበረሰቡም ኮሽታ በሠማ ቁጥር በተጠየቀው ዋጋ ከመግዛት ቢቆጠብ፤ ነጋዴውም አላስፈላጊ ዋጋ ከመጨመር ገበያውን በማረጋጋት ኢትዮጵያዊነቱን ቢያረጋግጥ ሲሉ አስተያየት ሠጥተዋል፡፡ ወይዘሮ አያል አይሸሽም በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የቀበሌ 14 ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮ አያል አንድ ኪሎ ስኳር 55 ብር መግዛታቸውን ነግረውናል፡፡ ዋጋው ቢጨምርም ስኳር እንደልብ ገበያ ላይ መገኘቱ በራሱ ጥሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡ መንግሥት ሸቀጦቹን ከቀረጥ እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንዲሆኑ መወሠን ብቻ ሳይሆን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እየሆነበት ያለውን መንገድም ሊፈትሽ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ባንቴ አንተነህ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴ ናቸው፡፡ አቶ ባንቴ ዘይት እና ስኳርን ጨምሮ ከቀረጥ እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆኑ መወሰናቸውን ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ዋጋቸው አለመቀነሱን ተናግረዋል፡፡ አቶ ባንቴ እንዳሉት መንግሥት ገበያውን ቢቆጣጠር እና በቂ ምርት ማስገባት ቢቻል ችግሩ እንደሚቀረፍ ጠቁመዋል፡፡ ችግሩን የሚያባብሱ ደላላዎችን መከላከል፣ ማኅበረሰቡም ከመደናገጥ ወጥቶ ቆም ብሎ ቢያስብ፤ በወሬ ከመፈታት ይልቅ እውነቱ ምንድን ነው የሚለውን ለመጠየቅ ጥረት ቢያደርግ፣ የተሻለ ገቢ አለኝ ብሎ በውድ ከመግዛት ቢቆጠብ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሙሀባው ሙላት መንግሥት ነፃ ገበያን በፈቀደው መሠረት ዋጋ ቀንሷል ባይባልም ምርት በተፈለገው መጠን በገበያ ላይ መገኘቱ ለማኅበረሰቡ እፎይታን ሠጥቷል ባይ ናቸው፡፡ በአቅርቦት ደረጃም ስኳር እና ዘይት ላይ ጅማሮው ጥሩ ቢሆንም ሌሎች ላይ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ አቶ ሙሀባው በደረሰኝ በሚሸጡ እና በሚገዙ ነጋዴዎች በተወሰደ ናሙና ዋጋ መቀነሱን ጠቁመው በርካታ ሸማቾች ግን በተሳሳተ ደረሰኝ ስለሚገዙ ዋጋው በሚፈለገው መጠን ላለመቀነሱ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በቀጣይ በአማራ ክልል በሚገኙ ደረቅ ወደቦች ላይ ምርት እንዲደርስ ለማድረግ እና የዋጋ ጭማሪውን ለማስተካከል የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ሙሀባው የንግድ ሠንሰለቱን በማሳጠር ጅምላ ነጋዴው ለጅምላ ነጋዴው ሳይሆን ለቸርቻሪው እና ለተጠቃሚው የሚያቀርብበት መንገድ እንደሚመቻች፤ የሽያጭ ሥርዓቱም ሕግን የተከተለ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አቶ ሙሀባው ደረሠኝ ዋስትና ወይም መተማመኛ ከመሆኑ ባሻገር የትርፍ ሕዳጉ ምን ያህል እንደሆነ ለማስላትም የምንጠቀምበት በመሆኑ ሁሉም ሰው በደረሰኝ እንዲገዛ እና እንዲሸጥ ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም በምርቱ ላይ ችግር ቢያጋጥም ለማስመለስ ብሎም ጉዳት ካደረሰም ለመካስ ደረሰኝ ጥቅሙ በርካታ ነው ባይ ናቸው፡፡ አቶ ሙሀባው በባሕር ዳር ምርት መዳረሻ ማዕከል ዘይት፣ ስኳር፣ ፓስታ እና መኮረኒ አምጥተው ሊያከፋፍሉ የሚችሉ ነጋዴዎች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ እንዲሁም ዩኔኖች እየተመለመሉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት ጅምላ ነጋዴዎች ድብብቆሻቸውን ትተው ለማኅበረሰቡ ወገንተኝነታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል፤ በተለይ ጥራት ያለው ምርት በማምጣት እና መንግሥት የሠጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ በመጠቀም ጤናማ የንግድ ሥርዓትን በመከተል ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ