ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክን የቁም እስረኛ ያረገው የሱዳን አለመረጋጋት፡፡

286
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ማንነታቸው እስካሁን ያልተለዩ ወታደራዊ ኀይሎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክን እና ሌሎች ሲቪል ባለስልጣናትን የቁም እስረኛ ማድረጋቸው ነው የተሰማው፡፡
በሲቪሉ እና ወታደራዊው ክንፍ ተብሎ በሁለት ጎራ የተከፈለው የሱዳን የሽግግር መንግሥት መረጋጋት ተስኖት ቆይቷል፡፡ የሁለቱ ጎራዎች የሥልጣን ሽኩቻ የሀገሪቱን ሰላም መመለስ ተስኖት ሱዳናውያንን ለአደባባይ ተቃውሞ ሰልፍ ዳርጓቸዋል፡፡
ለበርካታ ዓመታት ሱዳንን ይመሩ የነበሩትን አልበሽርን በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ገለል ያደረገው የሀገሪቱ ወታደራዊ ባለስልጣን ከዓመታት በኋላ አብደላ ሐምዶክንም በቤታቸው እንዳሉ የቁም እስረኛ ማድረጉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ከአልበሽር መውረድ በኋላ መረጋጋት ያቃታትን ሱዳንን ኢትዮጵያ ችግሮቿን በሰላማዊ መንገድ እንድትፈታ ትልቁን ድርሻ ወስዳ ነበር፡፡ በወቅቱ ታይቶ የነበረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ስምምነት እንዲደርሱ የኢትዮጵያ ድርሻ ከፍ ያለ ነበር፡፡
ሱዳን በሽግግር ወቅት ችግሮቿን በሰላማዊ መንገድ ትፈታለች ተብሎ ቢጠበቅም በሲቪሉ እና ወታደራዊ ክንፉ ያለው ሰጣ ገባ ጡዘቱ ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡
በኑሮ ውድነት መባባስና በሌሎች ችግሮች ሱዳናውያን ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ ሰነባብተዋል፡፡ በሀገሪቱ የሚታየው የኑሮ ውድነት አልበሽርን ከስልጣን እንዲወርዱ ሲያስገድድ ለሀገሪቱ ሰላም መምጣት ተስፋ የተጣለባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክንም ይሄው እጣ እንዲደርሳቸው አድርጓቸዋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ኢብራሂም አል ሼኪህ ፣ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሃምዛ ባላውል እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚዲያ አማካሪ ፋይሰል መሐመድ ሳላህ ይገኙበታል፡፡ የሱዳን ገዥ ሉዓላዊ ምክር ቤት ቃል አቀባይ መሐመድ አል ፊኪ ሱሌማን እና የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ገዥ አይማን ካሊድ እንዲሁ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ስማቸው ያልተገለፀ ሌሎች ባለስልጣናት መታሰራቸውንም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ባለፈው ወር በሀገሪቱ ከተሞከረው የከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ በሁለቱ ክንፎች ከፍተኛ ቅራኔ እንደነበር ነው የተዘገበው፡፡
ለረጅም ገዜ ከዘለቀ ተቃውሞ በኋላ በ2019 አልበሽርን ከስልጣን ያስወገደው ወታደራዊ መንግሥቱ በ2023 መጨረሻ ሰላማዊ ምርጫ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ የሲቪል መሪዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ ጀምሮ በሀገሪቱ የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት መቋረጡም ተሰምቷል፡፡ ወታደራዊ ክንፉ ወደ ካርቱም የሚያስገቡ መንገዶችንና ድልድዮችን ዘግቷልም ነው የተባለው፡፡
መረጋጋት የተሳናት ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የድንበር ይገባኛል ውዝግብ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ስምምነት አለመድረሷ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚያዋስናት አካባቢ የሱዳን ወታደር ወረራ መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለወንድማማች ሕዝቦች ክብር ሲባል ነገሮች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሰላማዊ እጆቹን እንደዘረጋም ይታወቃል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም ዕትም
Next articleከቀረጥ እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ የሆኑ የምግብ ሸቀጦች በገበያ ላይ የዋጋ መሻሻል እንዳልታየባቸው ሸማቾች እና ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡