
ደሴ፡ ጥቅምት 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “በበሬ ወለደ” የጠላት ወሬ ያልተፈቱት የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሀኪሞች ተረጋግተው የህክምና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ነው።
“ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንደሚባለው ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመልቀቅ የሆስፒታሉን መልካም ስም ለማጠልሸት እና የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስተጓጎል ሲሞከር እንደነበር የሆስፒታሉ የህክምና ዶክተሮች አስረድተዋል።
የገቡትን ሙያዊ ቃል ኪዳን በማክበር በማይመች ሁኔታም ውስጥ ሆነው ያለአንዳች ስጋት ቀን ከሌት ለታካሚዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሥራ ገበታቸው ላይ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ለአሚኮ ተናግረዋል።
ልዑል መስፈን (ዶክተር) የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው። ሆስፒታላቸው ከመደበኛ አገልግሎት በተጨማሪ ከደሴና አካባቢዋ የሚፈጠሩ ድንገተኛ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያለምንም ድካም አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ለተፈናቃይ ወገኖች እንዲሁም ህክምና ለሚያስፈልጋቸው የወገን ኀይል አባላት ተገቢውን ህክምና በመስጠት ላይ ስለመሆናቸው ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ሀኪሞች እንደሸሹ ተደርጎ ሲወራ የነበረው አሉባልታም ከጠላት የጥፋት ሀሳብ የመነጨ በሬ ወለደ እንደሆነ ዶክተር ልዑል አስረድተዋል። “በዚህ ወቅት ከወልድያ እና ከመርሳ የመጡ የህክምና ባለሙያዎችን ጨምረን ተጨማሪ አገልግሎቶችን እየሰጠን ነው” የሚሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ኅብረተሰቡ ከሀሰት የጥፋት ወሬዎች ራሱን መጠበቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የገቡት ቃልኪዳን በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ታካሚን ማገዝ እንዳለባቸው ሙያው ያስገድዳል ያሉት በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ክፍል አስተባባሪ ኀይለገብርኤል ፀጋው (ዶክተር) ያለምንም ስጋት ሥራቸውን እየሠሩ እንደሆኑ አስረድተዋል።
“ሙያዊ ሥነምግባርን አክብሬ ለሙያየ ታማኝ በመሆን እስከመጨረሻ ታካሚዎቼን እረዳለሁ” ብለዋል ዶክተር ኀይለገብርኤል፡፡
የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ሃይማኖት አየለ (ዶክተር) በበኩላቸው አሁን ላይ ሆስፒታሉ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ለጸጥታ አካላት እና ለማኅበረሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል። የጠላትን ፕሮፖጋንዳ ተቀብሎ ሆስፒታሉን ለማዘጋት በማሰብ አሉባልታ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲራገብ መታዘባቸውን የሚገልጹት ዶክተር ሃይማኖት ባለሙያዎች በአሉባልታው ሳይፈቱ ሌት ተቀን የህክምና ተግባራቸውን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ወቅቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ከስፔሻሊስት ሀኪሞች እስከ ጥበቃ ሠራተኞች የወቅቱን ሁኔታ ተገንዝበው በቁርጠኝነት የህክምና እርዳታ ፈላጊውን እያገለገሉ እንደሚገኙም ነው ያብራሩት።
ዘጋቢ፡- ግርማ ሙሉጌታ – ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m