
ጥቅምት 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ለአማራ ሕዝብ አዲሱ አይደለም፡፡ እንኳን ወገኑ ተነክቶበት፣ እህቱ ተደፍራ፣ በሬዎቹ ታርደው፣ “በጥቅምት ስንቅና ትጥቅህን ይዘህ ወረኢሉ ላይ እንድንገናኝ” ተብሎ ጥሪ በቀረበለት ጊዜም ቃሉን የጠበቀና ሀገሩን ያስከበረ ሕዝብ ነው፡፡
የእቴጌ ጣይቱ ልጆች ባሎቻቸውን አጀግነው ልጆቻቸውን መርቀው ሲሸኙ ለተመለከተ ያ የወረኢሉ ታሪክ እየተደገመ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የራስ ጉግሳ ወሌ ቤተሰቦች ከነካኳቸው እንቅልፍ የላቸውም፡፡ የፊታውራሪ ገብርየ ልጆች የሚያሸንፋቸው እምነት እና ፍቅር እንጂ የጠላት ጥይት አልነበረም፡፡
በጌምድሮች እንኳን የሚሮጥ ተኳሽን ተኝቶ የሚተኩስን ጠላት ይነጥላሉ፡፡
ከጓሳው ጋር እየተነጋገረ፣ ከጉና ጋር እያበረ፣ ከታላላቆቹ ጋር እየመከረ ጠላትን ለራሱ በሚገርመው ልክ የሚታገሰው የበጌምድር ሰው ለሀገሩ ክብር እንዲህ ይላል፡-
“ጎበዝ ጥይት ግዛ በወገብህ ደርድር፣
አልተደላደለም ገና ነው በጌምድር”
በእርግጥ ይህ ታሪክ ብቻ አይደለም ኑባሬም ጭምር እንጂ፡፡ አንዱ አስራ አንዱን ሲያነጥፈው በጆሮ ሰምተናል በዓይናችንም አይተናል፡፡ ከሕይዎታቸው በላይ ለተቋማቸው ሲሉ መስዋእትነትን የከፈሉ ጀግኖች መኖራቸውን አዳምጠናል፡፡ ይህ ትናንት በታሪክ ሳይሆን ዛሬም በኑባሬ የታየ የአማራ ሕዝብ ጀብዱ አንድ አካል ነው፡፡
“መሪ ከፈጣሪ ይመረጣል” ብለው የሚያምኑት አማሮች ልዩነት ቢኖራቸው እንኳን በጭንቅ ወቅት ለመሪዎቻቸው አንድ እና ምቹዎች ናቸው፡፡ ልዩነታቸው አንድነታቸውን አይፈታተነውም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠውን ለይተው ያውቃሉ፡፡ ለሀገራቸው በአንድ ይቆማሉ፡፡ ድንበሮቻቸውን በጋራ ይጠብቃሉ፡፡ ሉዓላዊነታቸው በጋራ ጥረታቸው እና መስዋእትነታቸው ከዘመን ዘመን ሳይደፈር ዘልቋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ጥንታዊ ነፃነት አርማ ፋኖነት ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ከጥንት እስከ አሁን ፋኖ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ በሰላም ጊዜ አራሽ፣ በጸሎት ወቅት ቀዳሽ፣ በጭንቅ ወቅት ተኳሽ እና በጠኔ ወቅት አጉራሽ ነው፡፡ ፋኖነት በዚህ ወቅትም የአማራ ሕዝብ የትግል ማዕከል ነው፡፡ በዚህ ወቅትም መሪው ክተት ወደ ወሎ ሲለው ከትቶ ጋይንት ላይ ተማምሏል፡፡
አርበኛ ፋኖ ጌታሰው ተስፉ በአማራ ፋኖ የገብርየ ብርጌድ በራስ ጋይንት ግንባር ሻለቃ መሪ ነው፡፡ የሕዝቡን ሰቆቃ እየተጋራን ዛሬም እንደጥንቱ ለአማራ ሕዝብ ነፃነት እና ለኢትዮጵያ አንድነት ዱር ቤቴ ካልን አንድ ዓመት ሞላን ብሎናል፡፡ የአማራ ሕዝብ እረፍት የሚያገኘው ጥንተ ጠላት ትህነግ ሲጠፋ ብቻ ነው ብለው የሚያምኑት እነ አርበኛ ፋኖ ጌታሰው ተስፉ የትኛውም መስዋእትነት ተከፍሎም ቢሆን ትህነግ የምትጠፋው አሁን እንደሆነ ያምናሉ፡፡
የክተት ጥሪውን ተቀብሎ እስከ እርስታችን ድረስ ዘልቆ የሚበጠብጠውን የሽብር ቡድን ለማክሰም ከአሁን የተሻለ አጋጣሚ የለም የሚሉት እነዚህ የፋኖ አባላት በእዝ ስር ሆነው የተሰጣቸውን ግዳጅ ሁሉ በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ነግረውናል፡፡
በሚጠሉን ልክ መጥላት፣ ባደረጉብን ልክ ማድረግ እና በመጡበት መንገድ መሄድ ወቅቱ የሚጠይቀው የትግል መርህ ነው የሚለው ፋኖ ጌታሰው ጠላትን ከወሎ ምድር ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ዳግም ለወረራ እንዳያስብ አድርገን ማስተማር ታሪካዊ ግዴታችን ነው ይላል፡፡ ለዚህ ሲባልም የክልሉ መንግሥት በሰጣቸው እውቅና መሰረት መንግሥት እና የወገን ጦር እዝ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በላቀ ገድል ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው፡፡
የክተት ዘመቻው ሕዝባዊ መሰረት ሊኖረው ይገባል የሚሉት የፋኖ አባላቱ የቻለ በመክተት፣ ያልቻለ በአካባቢው ሆኖ በመመከት እና ሃብት በማሰባሰብ ትግሉን መደገፍ እንዳለበትም የፋኖ አባላቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m