
ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/2012 ዓ/ም (አብመድ) የቤተ መንግሥት ዕድሳት በቀጣይ ሳምንት ማለትም ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም ተጠናቅቆ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረገ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶክተር) ዛሬ በቻይና መንግሥት ድጋፍ ግንባታው የሚካሄደውን የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ይህንን መግለጻቸውን ፋብኮ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የቤተ መንግሥት ዕድሳቱ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም ተጠናቅቆ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በማግስቱ ዓርብ ማለትም መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ቤተ መንግሥቱን እንደሚጎበኙም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ቅዳሜ እና እሑድ ደግሞ በዕድሜ ታላላቅ ዜጎች እና የጎዳና ተወዳዳሪዎች ቤተ መንግሥቱን እንደሚጎበኙም አስታውቀዋል።
ከሰኞ ማለትም ከጥቅምት 3 ቀን 2012ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ዜጋ 200 ብር በመክፈል ቤተ መንግሥቱን መጎብኘት እንደሚችልም ነው የተገለፀው።