“አለው ጠላቱን ተመለስ ዛሬ፣ ፈርቶ መመለስ የለም በዘሬ “

253
ጥቅምት 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ፍርሃት ካልፈጠረበት፣ በጀግንነቱ ከተመሰከረለት፣ በታሪኩ እንከን ካልተገኘበት፣ አድባር አክባሪ፣ ወገን አኩሪ፣ ወሰን አስከባሪ፣ እውነት መስካሪ፣ ለፍትሕ ተከራካሪ ከሆነ ሕዝብ ነው የተገኘኸው፡፡ የአስደናቂ እሴቶች ባለቤት፣ የገናና ታሪኮች አባት፣ የነጻነት ምልክት፣ የጨለማ መውጫ መብራት፣ ለተጨነቁት ደራሽ፣ ለተራቡት አጉራሽ፣ ላዘኑት እንባ አባሽ ከሆነ ሕዝብ ማህፀን ነው የፈለቅከው፡፡
ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ሽጉጡን የጠጣው፣ ጮማ በወረደበት፣ ጠጅ በተንቆረቆረበት፣ ማርና ወተት ባረሰረሰበት፣ ራዕይ በተነገረበት መልካም ጉሮሮ ባሩድ የለቀቀበት ከምንም በላይ ክብር እና ፍቅር ስለገባው ነው፡፡ እጅ መስጠት ስላልተፈጠረበት ነው፡፡ ለልጅ ልጁ ሞቶ መኖርን፣ ወድቆ ማቆምን ለማስተማር ነው፡፡ ሞቶ ስላኮራን፣ ወድቆ ስላቆመን ዛሬ ላይ በእርሱ ስም የተጠራው ሁሉ ደስ ይለዋል፡፡ የእርሱን ጀግንነት ለማውራት ይቀነዋል፡፡ ይሽቀዳደማል፤ የእርሱ ክንድ እንደሚያቃጥል እንጂ በጠላት እጅ እንደማይገባ ያወቀው ጠላት ደግሞ አንጀቱ እርር ይላል፡፡
እምዬ ምኒልክ ተቆጥተው የተነሱት፣ ወደ ዓድዋ የገሰገሱት፣ ለሀገር መሞት፣ ለሀገር ሕይዎትን መስጠት መታደል መሆኑን ስለሚያውቁ ነው፡፡ ዓድዋ ዛሬ ላይ የሚኮራበት፣ የሚሸለልበት፣ የሚፎከርበት፣ ደም እንደቦይ ፈስሶበት፣ አጥንት ተከስክሶበት፣ ሕይዎት ተገብሮበት ድል ስለተገኘበት ነው፡፡ የዛን ጊዜ አባቶቻችን ሆ ብለው ባይሄዱ፣ ምሽግ ባይረማመዱ፣ ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው ነጻነት ባያመጡ ኖሮ፣ ዓድዋ መፎከሪያ ሳይሆን ማፈሪያ ይሆን ነበር፡፡ እነርሱ ግን ሞትን አልፈሩም፣ ጠላትን አልሰጉም፣ እየገሰገሱ፣ እየተኮሱ፣ በጎራዴ የጠላትን አንገት እየቀነጠሱ ነጻነት አመጡ፣ ጥቁርን ከባርነት አወጡ፡፡ ከተራራው ላይ ሌላ የጀግንነት ተራራ ቆልለው መጡ፡፡
የቀደሙት አባቶች በባዶ እግራቸው፣ ልጆቻውን በቤት ከብቶቻቸውን በበረት ዘግተው፣ ስንቅና ትጥቅ በራሳቸው አዘጋጅተው ʺ ንጉሥ ሆይ ያስከትሉኝ ለሀገሬ ልሙትላት” እያሉ ይዘመቱ የነበሩት፣ በደማቸው ሀገር ያቆሙት፣ ማንነት፣ ሃይማኖት፣ ኢትዮጵያዊነት ስለሚጠራቸው ነው፡፡ መሸነፍ ስለሚያንገሸግሻቸው፣ ነጻነትን ማጣት እንቅልፍ ስለሚያሳጣቸው ነው፡፡ ልመነው እንዝመት፣ ለምነው እንሙት፣ ለምነው ጠላትን እንመክት ይላሉ፡፡
እኛ ሞቶ ያስከበረ፣ ሞቶ ያኖረ አባት እንጂ ፈርቶ የተዋረደ አባት የለንም፡፡ ዛሬ ላይ ሞተህ ልጆችህን፣ ሚስትህን፣ ሀገርህን ካለስከበርክ፣ ነገ ኖረህ ትሞታለህ፣ ራዕይ የሌለው ሕይዎት፣ ነጻነት የሌለው ኖሮ ከሞት አይተናነስም እና፡፡ የጠላት መቀለጃ፣ የግዳይ መለማመጃ ትሆናለህ፤ ሚስትህን እያዬሕ ታስደፍራለህ፣ ልጅህን በግፍ ታሰቃያለህ፣ እናትህ እንድትሞት ትፈቅዳለህ፡፡
ሞት ለማንም ነው፣ ዛሬም ኾነ ነገ አይቀርልህም፡፡ ሞትህ ትርጉም እንዲኖረው፣ ስምህን ከመቃብር በላይ እንዲያኖረው ግን ሞትህን ለክብርና ለፍቅር አድርገው፡፡ ሞታቸውን ለክብር ያደረጉት ኹሉ በታሪክ መዝገብ ላይ ይወሳሉ፤
ʺእሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው” እንዲሉ ጀግናው ዝም ሲል ሲነኩት የሚቃጠለው፣ ሲገፉት የሚወድቀው ጠላት ዛሬ ላይ መንደርህን ደፍሯል፤ ቀዬህን አርክሷል፣ ወገኖችህን ጨፍጭፏል፡፡ ሀብትህን አውድሟል፤ ተነስና እሳት መሆንህን አሳዬው፣ ጠላትህ ገለባ ነውና አቃጥለው፣ አክስለህ፣ በነፋስ ላይ አብነው፡፡ አንተ ነዲዱ የሚያቃጥል፣ ቁጣው የሚጥል፣ ጠመንጃው የሚነጥል፣ ሰይፉ የሚዘነጥል አባት ልጅ ነህና፡፡
ʺአይመጡም እንጂ ከመጡ ደፍረው
ጦርነት ጌጡ ውጊያ ጨዋታው ” የተባለለት አባት ልጅ ኾነህ እንዴት ርስትህን፣ ሚስትህን፣ ክብርህን አሳልፍህ ትሰጣለህ? እንዴት ጎልማሳን በርስቱና በሚስቱ አትምጡበት የሚለውን ብሒል ትረሳለህ? ማንንስ ትጠብቃለህ ? ዝመት፣ ትመም እንጂ፤ ልብ በል ያለ መስዋእትነት ነጻነት፣ ያለ ጀግንንት አሸናፊነት፣ ያለ ሞት ሰማዕትነት አለመኖሩን እወቅ፡፡ ሞተህ ለመኖር፣ ሞተህ ለማኖር፣ ገድለህ ለማስከበር ገስግስ እንጂ፤
ዓድዋን አያቶችህ ሠርተውልሃል፣ ከጠላት ወረራ አድነውሃል፣ ነጻነትን ከፍ አድርገውልሃል፣ ሠንደቅህን በኩራት አውለብልበውልሃል፣ ኮርተህ እንድትኖር፣ በዓለም ፊት እንድትከበር አድርገውሃል፤ አባቶችህ ካራማራን ደግመውልሃል፣ ጥጋብ የወጠረውን የጠላትን ልብ አስተንፍሰውልሃል፣ በዚያ በረሃ በዚያ ቃጠሎ ሠንደቋን ሰቅለው፣ አውልብልበውልሃል፣ አንተ የእነርሱን ታሪክ ብቻ እያወራህ እንዳትኖር ዛሬ ታሪክ ብራናውን ዘርግቶልሃል፣ እድል ሰጥቶሃል፤ ከአያቶችህና ከአባቶችህ ታሪክ አስከትልህ፣ የምትጽፍበት፣ የራስህን ዐሻራ የምታሳርፍበት፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ የምትጨምርበት አዲስ ብራና ተገልጦልሃል፡፡
በደም ቀለም የሚጻፍ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ፤ ብራናው ከደም ውጭ ሌላ ቀለም አይቀበልም፣ ብዕሩ ከደም ውጭ ሌላ ቀለም አይተፋም፣ ብዕሩ ደም ይተፋል፣ በብራናው ላይም ይጽፋል፤ ጠላትህን አጥፍተህ፣ በተገለጠው ብራና ላይ ጻፍበት፣ ታሪክህን ከትብበት፣ የተገለጠውን ብራና ሳትጽፍበት ብትቀር፣ ሀገርህን በጠላት ብታስወርር፣ ክብርህን ብታስደፍር ግን የአባቶች አጽም ይረግምሃል፣ የታሪክ ድርሳን ይዘልሃል፣ የሚመጣው ትውልድ ይረሳሃል፣ ያፍርብሃል፣ እንደ አባቶችህ ስምህ እንዲጠራ፣ የልጅ ልጅህ በስምህ እንዲኮራ ዛሬ ትመምና ታክ ሥራ፡፡
ʺየጀግናን እናት ማን ይደፍራታል
ያገኛት ኹሉ አንቱ ይላታል” እንዳለ ፎካሪው የምትከበረው የጀግና እናት ናት፣ ጀግና የወለደች በድልህ ትደሰታለች፣ ተከብራ ትኖራለች፣ በየጦር አውድማው ኹሉ እልል ትላለች፤ እሰይ እንኳንም ወለድኩህ እያለች ፈጣሪዋን ታመሰግናለች፣ እናትህ ተደስታ እንድታድር፣ በቀየዋ እንድትኖር ከፈለክ ተነስ ነፍጥህን አንሳ፡፡ ጠላትህን እጅ አስነሳ፡፡ ጠላትህ ሀገርህን ሲወራት፣ ልጅህን ሲደፍራት፣ እናትህን ሲያዳፋት ዝም ብለህ ካደረክ፣ ኖርኩ እንዳትል ሞተሃል እንጂ፡፡ የአንተ መኖር ማንነትህ በማስከበር፣ ሀገርና ሕዝብን በማኖር ላይ መመስረት አለበት፡፡ ተዋርዶ ከመኖር ተክብሮ መሞት ለታሪክ ይበጃል እና፡፡
ʺየፈሪን እናት ማን ያከብራታል፣
የመጣው ኹሉ ያዋርዳታል” የሚለው እንዳይደርስብህ፣ እናትህ እንዳትዋረድ፣ ልጅህ በስቃይ እንዳትገደድ ተጠንቀቅ፣ ሞተህ መኖርን እንደ አባቶችህ አሳይ፡፡ ሞተህ ለዘላለም ተከብር እንጂ ኖረህ ለዘላለም አትዋረድ፡፡ እናትህም፣ እርስትህም ይከበሩ ዘንድ ትመም፡፡
መነሻውን ከትግራይ ያደረገው ወራሪና ዘራፊ ቡድን የምፈልገው የመንግሥት አካላትን ነው የሚልህን አትስማው፣ በደርግ ዘመን የምፈልገው የደርግ ባለስልጣናትን ነው ብሎ አታልሎሃል፤ አሁንም ሊያታልልህ ነው፡፡ ደርግን ነው የምፈልገው ብሎ አሳልፈኸው የደርግን ባለሰልጣናት ሳይሆን የገደለው አንተን ነው፣ ያፈነቃለው አንተን ነው፣ ርስት የቀማው አንተን ነው፣ የውሸት ታሪክ የሠራው፣ ኹሉም ጠላቶች በአንድነት እንዲነሱብህ ያደረገው በአንተ ላይ ነው፡፡ ዛሬም አንተን ባይፈልግ ኖሮ ማይካድራ ላይ ሺዎችን አይገድልም ነበር፣ ጭናን የደም ምድር አያደርግም ነበር፣ አጋማሳና በሌሎች ሥፍራዎች አነጣጥሮ አይገድልህም ነበር፣ ጠላትህ የሚፈልገው ከቻለ አማራ የሌለባት ኢትዮጵያን መፍጠር ካለበለዚያም፣ ደካማና አቅመ ቢስ አማራ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ የሚፈልገው አማራን መግደል፣ ማፈናቀል፣ ከርስት መንቀል ብቻ ነው፡፡ አንተ ደግሞ የአባቶችህ ልጅ ኹን እምቢ አይሆንም በል፣ አይደረግም በለው፣ በየገባበት አስቀረው፣ መንደርና ቀዬህ እንደማያረማምድ፣ ጠላትን አሳልፎ እንደማይሰድ አሳዬው፡፡ ጎንደር ሲነካ፣ ወሎ ሲደፈር፣ ደጋጉ ወሎዬ ጦሙን ሲያድር ዝም ካልክ ታሪክ ይወቅስሃል፤ ማዕበል ኾኖ ሲመጣ፣ ማዕበል ኾነህ ጠብቀው፣ ዶፉን በላዩ ላይ ልቀቀው፣ በውሽንፍር አጨናንቀው፣ ምንጩን አድርቀው፤ ቀብሩን አርቀው፡፡
“አለው ጠላቱን ተመለስ ዛሬ
ፈርቶ መመለስ የለም በዘሬ ” በለው፣ በዘርህ ፈርቶ መመለስ፣ በጦር ሜዳ መለሳለስ የለም፣ ወደፊት መገስገስ፣ ምሽግ መደምስስ፣ ለተጨነቁት መድረስ ነው፡፡ ሂድ ወደ ወሎ ዝመት፣ ሂድ ወደ ደጋጎቹ ቀዬ የጋራ ጠላትን ደምስስ፣ ሂድ ለተራቡት ድረስላቸው፣ ሂድ ጠላትን አስለቅቅ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችህን ወደ ሞቀ ቤታቸው መልሳቸው፣ የአዘነውን ልባቸውን ጠግንላቸው፣ የፈሰሰውን እንባቸውን አብስላቸው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleደጀንነት በተግባር!
Next articleየሐሰት ፕሮፖጋንዳ – የሽብርተኛው ትህነግ የተለመደ እና ጊዜ ያለፈበት የጦርነት ስልት