ደጀንነት በተግባር!

285

ጥቅምት 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የበረታ ወጣት ነው፡፡ ቁልቁል ወርዶ ሽቅብ መውጣት በፍጹም አይሰለቸውም፡፡ በቀን እስከ ስድስት ሰዓት የእግር ጉዞ ወጥቶ መውረድ ከጀመረ አንድ ወር እያለፈው ነው፡፡ በስሌት እንጂ በስሜት የማይነዳ፣ ከዛሬው ፈተና ባሻገር የነገውን ፍስሃ የሚያስብ፣ ከራሱ በላይ ለወገኖቹ የሚኖር፣ ያየው ሁሉ “እንዳንተ አይነት ጥቂት በኖረን” የሚሉለት ወጣት በስፋት ጥጋቡ፡፡

እንደ እድል ሆኖ ምድራዊ ፈተና አንዳንዱን ልጅ ያለዕድሜው ታላላቆቹን አሳዳጊ ያደርገዋል፡፡ ወጣት በስፋት ጥጋቡም እንደዚያ ነው፤ የመከራ ቀንበር በርትቶባቸው ለባጁት ወገኖቹ ተስፋ ሆኗል፡፡ ከሎጀስቲክስ ኮሚቴ ታይቶ ምሽግ ውስጥ ይገኛል፡፡ ለተፈናቃዮች ችግር ደርሶ ወታደሩን አጉርሶ ወቅት የፈጠረባቸውን አካባቢያዊ ክፍተቶች ከጓደኞቹ ጋር በትብብር ይሞላሉ፡፡ ወጣቶቹን አስተባብሮ ወደ ኋላ አይቀርም ወደ ፊት ይመራቸዋል፡፡ የሠራዊቱን ስንቅ እና ትጥቅ ይሸከማሉ፤ ቁስለኛ ወደ ሕክምና ያደርሳሉ፤ የከተማዋን ነዋሪዎች ያስተባብራሉ፤ ውኃ ተሸክመው ምሽግ ለምሽግ እየዞሩ የፀጥታ ኀይሉን ያበረታታሉ፡፡ ይህ ሁሉ ኀላፊነት በወጣቶች ትከሻ የሚከወን ነው፡፡

ወጣት በስፋት ጥጋቡን እና ጓደኞቹን ከዚህ ሁሉ ልፋታችሁ መቼ ታርፋላችሁ? ስንላቸው ምላሻቸው “ጨርሰን ነፃ ስንወጣ” ነበር ያሉን፡፡

ከጋሸና እስከ ላል ይበላ፣ ከወልድያ እስከ ቆቦ፣ ከኮረም እስከ አላማጣ እየተጓዙ ከወገን ጦር ጀርባ ላለመጥፋት እና ብርቱ ደጀን ለመሆን ለራሳቸው ቃል ገብተዋል፡፡ ይህ እንደሚሆን ደግሞ ከጉና እስከ ጋይንት፣ ከደብረ ዘቢጥ እስከ አግሪት፣ ከመቄት እስከ አርቢት ባሉት አውደ ውጊያዎች ከፀጥታ ኀይሉ በኩል ባዩት ቁርጠኝነት እና ወታደራዊ ትጋት ሙሉ እምነት አድሮባቸዋል፡፡ “ነገ የተሻለ ይሆናል” የሚለው ወጣት በስፋት ጥጋቡ በፈተና ተስፋ መቁረጥ እና እጅ መስጠት አባቶቻችን አላስተማሩንም ነው ያለን፡፡

“የሰው ነፃነት አንነካም፤ የራሳችንም አሳልፈን መስጠት አንፈልግም” ብሏል፡፡ ሕዝባችንን ነፃ ለማውጣት በጋራ ቆመናል ነው ያለው፡፡ በሽሽት ጠላትን ማሸነፍ ስለማይቻልም ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማሸነፍ ብቸኛ ምርጫ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጿል፡፡

ወጣት በስፋት ጥጋቡ እና ጓደኞቹ የመቄት እና አካባቢው ነፃ መውጣት ለሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ነፃ መውጣት መነሻ ይሆናል እንጂ የትግላችን ፍፃሜ አይደለም ብለዋል፡፡ ከመቄት እና አካባቢው ጠላት ስለራቀ ነፃ ወጣን ማለት አይደለም የሚለው ወጣት በስፋት ጥጋቡ ጠላት ምንጊዜም ጠላት ነውና “ካልሄድን ይመጣሉ” ነው ያለን፡፡ የፀጥታ ኀይሉ በጀግንነት እና በትጋት ከሽብርተኛው ትህነግ ጋር እየተፋለመ ድል እያስመዘገበ መሆኑን እዛው ግንባር ድረስ ተሳትፈው አይተውታል፡፡

ወጣት በስፋት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ትግሉን ይቀላቀሉ፣ ያልቻሉ ደግሞ በሎጀስቲክ እና በሞራል መደገፍ አለባቸው ነው ያለው፡፡ ሕዝቡም በሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሳይናጥ እስከ ሕይዎት መስዋእትነት እየከፈለ ወገኑን ነፃ ለሚያደርገው የወገን ጦር ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡

በታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“የሰው ልጅ ነፃነትን ፈላጊ ነው፤ ነፃነት ግን በነፃ አይገኝም” የሕልውና ዘማቾች
Next article“አለው ጠላቱን ተመለስ ዛሬ፣ ፈርቶ መመለስ የለም በዘሬ “