
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ግዛቸው አሸባሪው ትህነግ አሁንም በክልሉ በወረራቸው አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ አረመኒያዊ ድርጊት እየፈጸመ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ንጹሃን ዜጎችን በመግደል፣ ሀብት እና ንብረታቸውን ደግሞ በመዝረፍ ለረሃብ እየዳረገ እንደሚገኝ ነው አቶ ግዛቸው ያነሱት፡፡
ባለፉት ወራት መላው የአማራ ሕዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች እና የጸጥታ ኀይል ጋር በመቀናጀት ይህንን የሽብር ቡድን በመታገል ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡ ትልቅ ገድል እየፈጸመ ይገኛልም ብለዋል፡፡ በዚህ ወቅትም አሸባሪው ቡድን ወረራ በመፈጸም የአማራን ህዝብ ለመጨፍጨፍ፣ ሀብት እና ንብረት ለመዝረፍ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታት ወጣቶች የተጠራውን የክተት ጥሪ ተቀብለው እየተቀላቀሉ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ሌሎች ወጣቶችም መንግስት እውቅና በሰጠው አደረጃጀት በመግባት አስፈላጊውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል መዘጋጀት ይገባልም ብለዋል፡፡
አቶ ግዛቸው እንዳሉት የኅልውና ዘመቻው ውጤታማነት ማኅበረሰቡ ከስሜታዊነት በመውጣት መንግሥት የሚስቀምጣቸውን አቅጣጫዎች መከተል ይገባል፡፡ የክተት ጥሪው በጦር ግንባር ብቻ መሳተፍ አለመኾኑን የገለጹት አቶ ግዛቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በመደገፍ፣ ስንቅ በማቅረብ፣ የገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ማገዝ ይገባል ብለዋል፡፡ ከሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችም ለሕልውና ዘመቻው ለሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ለዚህ አላማ ተብሎ በተከፈተው የሂሳብ ቁጥር ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በተለያየ መንገድ ሰርጎገቦችን ወደ ማህበረሰቡ በማስረግ የተለመደ የማደናገር ስራ እየሰራ በመኾኑ ተከታትሎ ማክሸፍ እንደሚገባ ሃላፊው አሳስበዋል፡፡ አሸባሪው ቡድን በሕቡዕ ባቋቋመው የፌስቡክ ቡድን የሚያሰራጨውን ሀሰተኛ መረጃ ማክሸፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግስትን የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ማዕከላትን በመረጃ ምንጭነት መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m