
ባሕር ዳር: ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ እና በአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ረዳት ኀላፊ ሳራህ ቻርለስ ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ዛሬ ጠዋት ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጋር የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በውይይታቸውም አሸባሪው ትሕነግ ባደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ምን እንደሚመስል እና በቀጣይ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ተነጋግረናል ብለዋል፡፡
አምባሳደሯ በሰጡት መግለጫ መሠረት ጦርነት በሚካሄድባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ንጹኃን ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፡፡ በጦርነት፣ በርሃብ እና አለመረጋጋት ጊዜ የሚያጋጥም ችግር ድንበር የለውም ያሉት ጊታ ፓሲ የሕዝቡን ሰቆቃ ለማስቀረት ለሚፈጠረው ቀውስ እልባት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ያለምንም ልዩነት ድጋፍ ለማድረግ አሜሪካ ቁርጠኛ መሆኗንም አስታውቀዋል፡፡
በአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ረዳት ኀላፊ ሳራህ ቻርለስ በኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው የብዙኃን ሰቆቃ አሳስቦናል በማለት ተናግረዋል፡፡ ጦርነት እየተካሄደባቸው በሚገኙ አካባቢዎች ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ በርካቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተረድተናልም ነው ያሉት፡፡ የምግብ እጥረት፣ የመጠለያ ችግር፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ እና የሕክምና ችግር ማጋጠሙን ጠቅሰዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ እና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ጋር በአማራ ክልል የሚሠሩ አጋሮች እንዳሏቸው ያነሱት ረዳት ኀላፊዋ ዛሬ ባሕር ዳር የተገኙት በክልሉ የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
በአማራ ክልል የተወረሩ አካባቢዎችን ጨምሮ ድርጅታቸው በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚደረገውን ድጋፍ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ የእኛ ሠራተኞች ከዚህ ያሉት ሕይወት የማዳን ተልዕኮ ስላለን ነው፤የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማገልገል እና ፍላጎታቸውን ለማሟላት ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ