
ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ካለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራ እና አፋር ክልሎች መጠነ ሰፊ ወረራዎችን ፈጽሟል፡፡ የሽብር ቡድኑ አባላት በወረራ በያዟቸው አካባቢዎች እየፈጸሙት ያለው የወንጀል ድርጊት ለዘመናት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብረው ስለመኖራቸው ሁሉ የሚያጠራጥር ሆኗል፡፡ ከኢትዮጵያዊያን እሴት እና ባሕል ባፈነገጠ መልኩ ነውር የፈጸሙት የሽብር ቡድኑ አባላት ጥላቻ ምን ያክል እንዳናወዛቸው አመላካች ነው፡፡
የትህነግ ሽብር ቡድን አባላት ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ፣ አመለካከታቸው የዘቀጠ እና ድርጊታቸው ሁሉ የትግራይን ሕዝብ ስምና ክብር ያዋረደ ሆኖ በታሪክ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ቀልሟል፡፡ በሰለጠነ ዘመን በሕጻናት ትምህርት ቤት ውስጥ ጸያፍ ስድቦችን የከተቡ፣ ለእናቶች የማያዝኑ እና ልጃገረዶችን አስገድደው የደፈሩ አረመኔዎች ሆነዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ግልጽ የወጣው ጉዳይ ወረራው ሕዝባዊ መሆኑ ነው፡፡ አሸባሪው ቡድን ትግራይ ውስጥ የሚገኝን የሰው ዘር ሁሉ ለወረራ አሰማርቶ በአማራ ክልል አሰማርቷል፡፡ በዚህም መጠነ ሰፊ ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት ደርሷል፡፡
በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎችም ወጣቶች ወረራውን ለመመከት ሕዝባዊ ማዕበል ፈጥረው አኩሪ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡ እስከ ሕይዎት መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖችም አሉ፡፡ በፍላቂት ገረገራ ከተማ አስተዳደር ያገኘናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም ለፀጥታ ኀይሉ ደጀን ሆነው እየደገፉ መሆኑን አስተውለናል፡፡
“የሽብር ቡድኑ ከገባበት ሐምሌ 30/2013 ዓ.ም ጀምሮ የፍላቂት ገረገራ ከተማ አስተዳደር ነፃ እስከወጣችበት ጳጉሜን 5/2013 ዓ.ም ድረስ የፈጸመውን ነውር ያየ ሕዝብ ያለምንም ጥርጥር ለፀጥታ ኀይሉ ደጀን ይሆናል” ያሉን የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሙሉየ እንዳለው ናቸው፡፡ የሽብርተኛው ትህነግ አስከፊነት ለተወሰነ የኢትዮጵያ ክፍል አይደለም ያሉት አቶ ሙሉየ “የሽብር ቡድኑ አይሳካለትም እንጂ ቢሳካለት ዓላማው ኢትዮጵያን መበተን ነው” ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሽብርተኛው ትህነግ እስትንፋስ እስኪቋረጥ ድረስ በጋራ መቆም አለበት ብለዋል፡፡
አቶ ሙሉየ ሕዝቡ የአሸባሪው ትህነግ ሴራ ገብቶት ተደራጅቶ ከፀጥታ ኀይሉ ጎን በመሰለፍ ደጀንነቱን እያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመው ከዚህ መካከል የአሸባሪውን ቡድን ዓላማ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እያስፈጸሙ ያሉ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጠላትን ፊት ለፊት ገጥሞ ማሸነፍ እንጂ በሰርጎ ገቦች ሴራ ተጠለፎ ማፈግፈግ ታሪኩ አይደለም ብለዋል አቶ ሙሉየ፡፡
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ እና የሎጀስቲክስ አስተባባሪ ኮሚቴ አባሉ አቶ ተንሳይ ኀይለሚካኤል ሽብርተኛውን ትህነግ በግንባር እየተፋለመ ላለው የፀጥታ ኀይል ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ተንሳይ ወጣቶች ተደራጅተው በግንባር ልዩ ልዩ ወታደራዊ ድጋፎችን ጭምር እያደረጉ መሆኑንም ነግረውናል፡፡

አቶ ተንሳይ “የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ለወረራ ሲመጡ እኛ ቆመን የምንወረርበት ጊዜ አልፏል” ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ሠራዊቱ ሊሞትለት የሚገባ ሕዝብ እንዳለ እንዲያስብ አድርጎታል የሚሉት አቶ ተንሳይ እስከ ሕይዎት መስዋእትነት የሚዘልቅ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
አቶ ተንሳይ ነፃ በወጡ አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች ከጋይንት እና ከደብረ ታቦር ድረስ በመምጣት ሠራዊቱን በሎጀስቲክስ በመደገፍ አርአያ እንደሆኗቸው ጠቅሰዋል፡፡ ቀሪው ወጣት እና የኅብረተሰብ ክፍልም የህልውና ዘመቻውን ዳር ቆሞ ከመመልከት ትግሉን መቀላቀል እና የሽብር ቡድኑን መደምሰስ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የጠላትን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ተቀብሎ ሕዝብን ማሸበር ታሪካዊ ስህተት መሆኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጭዎቹ የጠላት አቅም በቅርብ ስለታየ ሁሉም በወረራ የተያዙ አካባቢዎች ነፃ የሚወጡበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ