
ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥቷል።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት የሰጠው መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል:-
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ደሴ ከተማን ዒላማው አድርጎ የሚያቅዳቸው በርካታ የጥፋት ሥራዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው።
በሁሉም ግንባሮች በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ለህልውናቸው በተሰለፉት የክልሉ ወጣቶች የሚደርስበት ከባድ ኪሳራ ሩቅ እንደማያስኬደው ግልጽ ሆኗል።
የደሴ ከተማ ላይ ያቀደው ጥፋትም ይህንኑ ሽንፈቱን በጥፋት ሥራ ለመሸፈን ማቀዱን ያሳያል። ኅብረተሰቡም የዚህን ሽብር ቡድን እኩይ ዓላማና እቅድ በመረዳት ሀገርን ለመበታተን አቅዶ የተነሳውን የጥፋት ኃይል ሴራ ማክሸፍ ይገባዋል።
የሽንፈት ገፈትን እየቀመሰ የሚገኘው የሽብርተኛው ቡድን በደሴ ብዙ ሠራዊት ሊኖር ይችላል በሚል በተጨማሪም ፋኖ የከተማ የውጊያ ስልትን ለማካሄድ ሊዘጋጅ ይችላል የሚል ግምትን በማሳደር ሰርጎ ገቦችን በመጠቀም በከተማዋ የመብራት መስመሮችን ለማቋረጥ እና በደሴ የሚገኘው የፀጥታ ኃይል ላይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለማሳደር ማቀዱን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።
በከተማዋ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊትም ኾነ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከመረጃ እንዲርቅ ማድረግንም በእቅዱ ይዟል። ሐሰተኛ መረጃዎችንና ምስሎችን በስፋት በማሰራጨትም የሠራዊቱንና አጠቃላይ የፀጥታ ኃይሉን ሞራል ለማዳከም ያስችሉኛል በሚል የያዛቸው እቅዶች መኖራቸው ተደርሶበታል።
ይህ የጥፋት ቡድን ሀገርን ማሸበር ዋና ዓላማው መሆኑን የሚያሳይ ነው። የአማራ ክልል ሕዝብና መላው ኢትዮጵያውያን የሽብር ቡድኑ ትህነግ ያቀዳቸውን የማወናበጃና የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተግባራት የማወክ እንቅስቃሴን ቀድሞ በመረዳት ሰርጎ ገቦችን በማጋለጥና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ እንደስካሁኑ ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት መልእክት ያስተላልፋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m