
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ላቀ ጥላዬ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ስናን ወረዳ በ1960 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ የሆኑት አቶ ላቀ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከወረዳ እስከ ዞን ባሉት የተለያዩ ቦታዎች በኀላፊነት ሕዝብን በቅንነት እንዳገለገሉ የሕይወት ታሪካቸው ያመላክታል፡፡
አቶ ላቀ የስናን ወረዳን ሕዝብ በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆንም የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት መሳተፋቸውን እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ምሥራቅ ዕዝ በሻለቃ ማዕረግ የአስተዳደር ዘርፍ ተመድበውም ሠርተዋል፡፡
አቶ ላቀ ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ የአማራ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ድጋፍ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ኀላፊ በመሆን የክልሉ ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጾ እንዲያበረክት በትጋት ሠርተዋል፡፡ በተለይም ሕዝቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግ እና ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ነዋሪዎችንና ምሁራንን በማወያየት የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዙ እና የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ሠርተዋል፡፡
ባለትዳርና የሦስት ሴት ልጆች አባትና የሀገር ባለውለታ የነበሩት የአቶ ላቀ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ቤተሰቦቻቸዉ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸዉ፣ የወረዳ፣ የዞንና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በደብረማርቆስ ከተማ አብማ ማርያም ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ተገልጿል።
መረጃው፡- የምሥራቅ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m