
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ አሸባሪው ትህነግ በአፋርና አማራ ክልሎች ውስጥ ንጹሃንን መግደሉን፣ ማፈናቀሉና ሀብት ንብረት መዝረፉንና ማውደሙን አስታውሰዋል። “ቡድኑ ከመንግሥት ንብረት በላይ የግለሰቦችን ሀብትና ንብረት እየዘረፈ ያለ ግፈኛ የሽብር ቡድን ነው” ሲሉ የአረመኔነቱን ጥግ ገልጸዋል።
ሊታገዙ እንጂ ሊዘረፉ የማይገባቸውን አቅመደካማ አረጋዊያንን እና ማየት የተሳናቸው አካል ጉዳተኞችን ሁሉ ሳይቀር እየዘረፈ ያለ ከሰብዓዊነት የራቀ መሆኑንም አስረድተዋል። ቡድኑ ከቀድሞው በከፋ መልኩ ከሰብዓዊነት ርቆ የአረመኔነትና የአውሬነት ባህሪ ተላብሶ ያገኘውን ሁሉ በኢሰብዓዊነት እየጨፈጨፈ ያለው ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስለገባ እንደሆነ አመልክተዋል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሸባሪው ትህነግ አውሬ መሆኑን ተረድቶና ተገንዝቦ ቡድኑን ለመደምሰስ በሚደረገው እንቅሰቃሴ ግንባር ቀደም ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ቡድኑ ኢትዮጵያን ባስተዳደረበት ወቅት በዙ በደሎችን ማድረሱን ጠቅሰው፤ ዘረፋና ዜጎችን በማስመረር ለስደት መዳረግ ተግባሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
ዘራፊው ቡድን የጊዜ ጉዳይ እንጂ አሁን እየፈፀመ ያለው አረመኔያዊ ድርጊት በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የሚመከት መሆኑን ገልፀዋል።
‘ታላቋን ትግራይን ለመመስረት ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት’ ብሎ ለተነሳው አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እንዲጥል የአፋር ሕዝብ እንደማይፈቅድለት ገልጸዋል።
ቡድኑ በአፋር ሕዝብ የተባበረ ክንድ ኪሳራ እየደረሰበት እንደሚገኝም አቶ አወል አርባ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m