
አዲስ አበባ: ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው የተለያዩ የውጭ ሀገራት መሪዎች አዲሱን የኢትዮጵያ መንግሥት ምሥረታ ተከትሎ ለመሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት መላካቸውን አንስተዋል። ከሀገራቱ መካከል የፖላንድ ፣ የቤልጂየም፣ የሩሲያ፣ የኦማን፣ የቻይና ፣ የጀርመን ፣ ፣የሰሜን ኮሪያ፣ የቬንዙዌላ እና ሌሎች ሀገራት እንደሚገኙበት ቃል ዐቀባዩ አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን አፍሪካ ሕብረት ምርጫውን በመታዘብ ለነበረው ሚና ማመስገናቸውን አስረድተዋል። ከጉባኤው ጎን ለጎን ከየሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ምክከር አድርገዋል ነው ያሉት።
የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንትን ሕብረቱ በጉባኤው መርጧል ብለዋል። አጀንዳ 2063 ለማሳካት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ምክከር በማካሄድ ስብሰባው በስኬት ተጠናቋል ነው ያሉት። በሕብረቱ ጉባኤ እንደተለመደው ኢትዮጵያ ያላትን ዓለም አቀፍ ስብሰባ የማስተናገድ አቅም ማሳየቷን የተናገሩት አምባሳደር ዲና 39ኛው መደበኛ የሚኒስትሮች ስብሰባ በስኬት መጠናቀቁንም አስገንዝበዋል።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሚገባው ልክ ከመዘገብ ይልቅ ባልተገባ መንገድ ሽፋን እየሰጡ መሆኑ ያሳዝናል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል አቶ ደመቀ መኮንን ከስሎቫኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናዚ ሎገር ጋር በስልክ ባካሄዱት ውይይት አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጵያ ላይ እየፈጸመ የሚገኘውን ጉዳት አብራርተውላቸዋል። አቶ ደመቀ አሸባሪው ትህነግ በአማራ እና አፋር ክልሎች ንጹሐንን በመጨፍጨፍ፣ ንብረት በመዝረፍና በማውደም እኩይ ድርጊቱን መፈጸሙን አስረድተዋቸዋል።
የተመድ ሠራተኞችን በጥፋታቸው እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ከሀገር እንዲወጡ መደረጉን አቶ ደመቀ ተናግረዋል። አሸባሪው ትህነግ ለእርዳታ የገቡ 420 መኪኖችን በማገት ለጦርነት እያዋላቸው መሆኑን መግለጻቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
ስሎቫኒያ የወቅቱ የአውሮፓ ሕብረት ሊቀመንበር መሆኗን የተናገሩት ቃል ዐቀባዩ ይህን ታሳቢ በማድረግ አቶ ደመቀ የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ አቋም መያዙን አብራርተውላቸዋል።
አቋሙ አድሎ ያለበት እና መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የሳተ እንደሆነ መግለጻቸውን አምባሳደር ዲና አስረድተዋል።
የስሎቫኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የሕብረቱ ፍላጎት ለሲቪሎች እርዳታ ማድረስ መሆኑን እንደገለጸ አንስተዋል።
አምባሳደር ዲና የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ኢትዮጵያ በመገኘት ከአቶ ደመቀ ጋር ምክከር ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ