አሸባሪው የትህነግ ኃይል በዛሪማ ከተማ በሚገኘው መስጂድ ላይ የፈጸመውን ውድመት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አወገዘ።

228

ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ኃይል በሰሜን ጎንደር ዞን አዲአርቃይ ወረዳ ዛሪማ ከተማ በሚገኘው መስጂድ ላይ በከባድ መሳሪያ ያደረሰውን ውድመት እንደሚያወግዝ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ኃይል በአማራ ክልል ላይ እየፈጸመ በሚገኘው ጦርነት በሕዝቦች ሕይወት ላይ አስከፊ ግድያ እና መፈናቀል በየቀኑ የሚሰማ መርዶ ሆኖ ቀጥሏል ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ በዜጎች፣ በሕዝብ መገልገያ ተቋማትና መሠረተ ልማቶች ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት አሳዛኝ ነው ብሏል።

በሰሜን ወሎ፣ በዋግ ኽምራ፣ በደቡብ ወሎ አካባቢዎች በርካታ መስጂዶችና መድረሳዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ አማኞችም ተጎድተዋል ያለው መግለጫው ዝርዝሩ ወደፊት በጥናት የሚገለፅ መሆኑንም አመላክቷል።

ምክርቤቱ በመግለጫው አሸባሪው የትህነግ ኃይል ጉዳት ያደረሰበት ዛሪማ ከተማ የሚገኘዉ ጥንታዊ መስጂድ በርካታ ዓመታት እድሜ ያለው እና በቅርቡ በዘመናዊ መንገድ ተገንብቶ እንደነበርም ገልጿል።

የዛሪማ መስጂድ ጥቅምት 7/2014 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት 30 አካባቢ በአሸባሪው የትህነግ ኃይል በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ከፍተኛ ዉድመት እንደደረሰበት ከአካባቢው ኅብረተሰብ እና ከወረዳዉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የሥራ ኃላፊዎች በደረሰው መረጃ ለማረጋገጥ መቻሉንም በመግለጫው አመላክቷል፡፡

ከፖለቲካ ጋር አንዳች ግንኙነት በሌላቸዉ የእምነት ቤቶች ላይ የሚፈፀመዉን አውዳሚ ተግባር የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጽኑ ያወግዛል ብሏል፡፡

ወደፊት መስጂዱን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

መንግሥት የሕዝቦችንና የእምነት ቤቶችን ደኅንነት እንዲያስጠብቅም የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጠይቋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ትህነግ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ190 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ።
Next articleየአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም የተሳሳተ መሆኑን ማስገንዘብ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።