
ደሴ: ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ደሴ ከተማ በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ነዋሪው በተረጋጋ ሁኔታ እንደተለመደው ሁሉ ከማለዳ ጀምሮ ወደ መደበኛ ሥራውና ግብይቶችም በተረጋጋ ሁኔታ እየተካሄዱ እንደሆነ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ገልጸዋል።
አቶ እንድሪስ ሙሐመድ የደሴ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ባልተጨበጠ መረጃ “በዚህ ገቡ በዚህ ወጡ” በሚል ሽብር በሚነዙ ሰርጎ ገቦች ኅብረተሰቡ ሳይደናገር በማለዳው ወደ መደበኛ ተግባሩ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የሽብር ወሬ የሚነዙትንም ወጣቱና የከተማው አስተዳደር እየተቆጣጠረ ከተማውን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ሌላው የደሴ ከተማ ነዋሪ ኃይለልዑል ተፈሪ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚለው ደሴ ከተማ ላይ አይሰራም ሲል ይገልፃል። የደሴ ነዋሪም በምንም አሉባልታ ሳይፈታ በማለዳው መደበኛ ተግባሩን እያከናወነ መሆኑንም ተናግሯል።
❝እዚሁ በጉያችን ተሸጉጠው በወሬ ሊንጡን የሚያስቡትን እየታገልን በቀጣይም የከተማችን ፀጥታ አስከብረን በተረጋጋ ሁኔታ እንቀጥላለን❞ ነው ያለው።
አቶ ይርጋሰው ዓለም ሰሞኑን አሸባሪው ትህነግ የሚለቀውን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ተረድቶ አክሽፎታል ብለዋል።
የአካባቢው ወጣቶችና ከተማ አስተዳደሩ ባከናወኑት የተቀናጀ ሥራ ኅብረተሰቡ በተረጋጋ ሁኔታ ከማለዳው ጀምሮ የዕለት ከዕለት ተግባሩን እያከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይም ኅብረተሰቡ በንቃት አካባቢውን እየጠበቀ የተረጋጋ ኑሮውን መቀጠል ላይ ማተኮር እንዳለበትም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ግርማ ሙሉጌታ -ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ