በአማራ ክልል ባለፈው በጀት ዓመት መጠናቀቅ የነበረባቸው 17 ድልድዮች ወደ 2012 በጀት ዓመት ተላልፈዋል ተባለ፡፡

132

ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/2012 ዓ/ም (አብመድ) የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የ2012 በጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያዬ ነው፡፡ በውይይቱ ላይ እንደተገለጸውም በየወረዳዎች የተጀመሩ የድልድይ ግንባታዎች ተጓትተዋል፤ በክልሉ በ2011 በጀት ዓመት መጠናቀቅ ሲገባቸው 17 የድልድይ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ወደ 2012 በጀት ዓመት ተሸጋግረዋል::

የትራፊክ አደጋም በታሰበው ልክ መቀነስ እንዳልተቻለ የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል:: በቢሮው በ2011 በጀት ዓመት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል ቢኖርም የትራፊክ አደጋን መቀነስ ላይ እጥረት መኖሩ ነው የተገለጸው፡፡

ለአብነትም በ2011 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ 1 ሺህ 109 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል ነው የተባለው::

የመናኸሪያ ግንባታዎች መከናወናቸው ጥሩ ቢሆንም የሚሰጠው አገልግሎት አርኪ አለመሆኑም ነው የተገመገመው::

የአብክመ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ እንዳሉት በ2012 በጀት ዓመት የገጠር መንገድ ተደራሽነት የተጀመሩ መንገዶችና ድልድዮች የሚጠናቀቁበትና የትራንስፖርቱን ዘርፍ ለማዘመን አዳዲስ ሥራዎች የሚጀመሩበት ነው::

የቢሮ ኃላፊው እንደገለጹትም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስም የአሽከርካሪ ተቋማትን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ -ከደብረ ብርሃን

Previous articleበአሜሪካ በተፈጸመ የአየር ጥቃት የሶማሊያ አርሶ አደሮች መገደላቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ማረጋገጡን ገለጸ፡፡
Next articleበቻይና ቤጂንግ ወታደራዊ ትርዒት እየቀረበ ነው፡፡