❝ነብዩ መሐመድ የሚወዷትን ሀገር እንውደዳት፤ እናክብራት❞ ፕሮፌሰር አደም ካሚል

425
ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በሁሉም ነገር የተወደደች፣ የተመረጠች፣ የተከበረች፣ የቀደመች ሀገር ናት፡፡ ነብዩ መሐመድ የሚወዷት፣ መልካም ምድር፣ የታማኞችና የደጎች፣ ፍትሕ የሚያውቁ ሕዝቦች ሀገር እንደኾነች የተናገሩላት፣ አምነው መልእክተኞችን የላኩባት፣ እርሷን አትንኳት ያሉባት ሀገር ናት -ኢትዮጵያ፡፡
ኢትዮጵያም የወደዳትን ነብይ በዓል በድምቀት ታከብራለች፡፡ በድምቀት ከምታከብራቸው በዓላትም አንዱ ነው- መውሊድ፡፡
የነብዩ መወለድ የዓለምን አካሄድ ቀይሮታል፤ ብርሃንም ለዓለም መጥቷል ይላሉ የሃይማኖቱ አባቶች፤ ነብዩ መሐመድ አዲስ ሕግጋትን አጽድቀዋል፡፡
ከሰማይ ከአሏህ ዘንድ የተሰጣቸውን መልእክትም በምድር ላይ ፈጽመዋል፡፡
ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሮፌሰር አደም ካሚል መውሊድን ስናከብር ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ያለንን ትስስርና ታሪክ ለማስታወስ ነው ብለዋል፡፡ በእስልምና አስተምህሮ ውስጥ ከእርሳቸው በፊት በርካታ ነብዮች ነበሩ ግን አንዳቸውም እንደ ነብዩ መሐመድ ከአሏህ ጸጋ የተሰጣቸው አልነበሩም፡፡ ነብዩ ሙሐመድ ግን የነብዮች ኹሉ መጨረሻ፣ ከነብዮች ሁሉ ታላቅ መልእክት ይዘው የመጡ፣ የዓለምን መልክ የለወጡ ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር አደም ማብራሪያ የሰው ልጅ ምድርንና በምድር ያሉትን ኹሉ እንዲገዛ ተመረጠ፡፡ አዛዥም እንዲኾን ተፈቀደለት፡፡ የሰው ልጅ ግን ስህተት ሠራ፡፡ መከራም ኾነ፡፡ የተሳሳተውን የሰው ልጅ ለመመለስ፣ የተበላሸውን የምድር አካሄድም ለማስተካከል ነብዩ መሐመድን መልእክተኛ አድርጎ አሏህ ላካቸው፡፡ እርሳቸውም የተበላሸውን የሚያስተካክሉ የመጨረሻው የአሏህ መልእክተኛ ናቸው ነው ያሉት፡፡
የነብዩ የመወለጃ ጊዜ ደረሰ፡፡ ተፀነሱም፡፡ አባታቸው ግን የተበላሸውን ዓለም የሚያስተካክሉትን ልጃቸውን ሳያዩ ገና ሳይወለዱ አለፉ፡፡ እሳቸውም ተወለዱ፡፡ እናታቸውም በስድስት ዓመታቸው አለፉ፡፡ ነብዩንም ኢትዮጵያዊት በኾነች ሴት አደጉ ነው የሚሉት፡፡ ኢትዮጵያዊት እመቤትም በጅብሪል ረዳትነት ታሳድጋቸው ጀመር፡፡ ነብዩም ይህችን እመቤት ከቤተሰቦቼ ቀጥላ የምትቀመጠው ሴት ናት ይሏታል ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ነብዩን በማሳደግ ረገድ ኢትዮጵያውያን ታሪካቸው እዛ ጋር ይጀምራል ነው የሚሉት፡፡
ፕሮፌሰር አደም እንዳሉት ነብዩም መልእክታቸውን ይፈጽሙ ጀመር፡፡ የተዛባውን ፍትሕ ያስተካክሉ ጀመር፡፡ በመካም አዲስ ሕግ አወጡ፡፡ ከአሏህ የተሰጣቸውን መልእክትም አወጁ፡፡ ጠላቶቻቸውም ተነሱባቸው፡፡ መልእክታቸውንም እንዳይፈጽሙ እንቅፋት ኾኑባቸው፡፡ መልእክተኞቻቸውንም ከክፉ ሰዎች እጅ ለመጠበቅ ሲሉ የእውነት ምድር ወደ ኾነችው ምድር ሂዱ ደገኛ ንጉሥ አለ ብለው ላኳቸው፡፡ መልእክተኞቹም ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ኢትዮጵያዊ ንጉሥም መልእክተኞችን ተቀበለ፡፡ በኢትዮጵያም በክብር አስቀመጣቸው፡፡
ነብዩ ሙሐመድ ከአሏህ የተሰጣቸውን መልእክት መሠረት እስኪጥሉ ድረስ ሐበሾች ከጎናቸው ነበሩ፡፡ ለዚያም ነው የመላው ዓለም ሙስሊም የኢትዮጵያ እዳ አለበት የሚባለው ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፡፡ ነብዩም ኢትዮጵያውያንን ይወዱ ነበር፡፡ የዓለም ሙስሊም ኢትዮጵያን ይወዳል ነው ያሉት፡፡
ፕሮፌሰር አደም ❝ነብዩ ሙሐመድ የሚወዷትን ሀገር እንውደዳት፣ እናክብራትም ነው❞ ያሉት፡፡
ፕሮፌሰር አደም ነብዩ ሙሐመድ ለሰው ልጅ አይደለም ለእንስሳት መብት የቆሙ ናቸው ብለዋል፡፡ አሁን ግን የሰው ልጅ ለሰው ክብር ሲነፍግ ይታያል፡፡ ሰውም የነብዩን አስተምሕሮ መተግባር አለበት፤ ቃላቸውን መጠበቅ፣ ሕግጋቱንም ማክበር አለበት ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየመውሊድ በዓል በግንባር…
Next articleሽብርተኛው ትህነግ ሙሉ በሙሉ እስኪደመሰስ ከፀጥታ ኀይሉ ጎን በመሰለፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የፍላቂት ገረገራ ከተማ እናቶች ተናገሩ፡፡