የመውሊድ በዓል በግንባር…

270
ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) 1496ኛው የነብዩ ሙሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡ የሕልውና ዘመቻ ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የጽናት ተምሳሌት የኾነውን የመውሊድ በዓል በጽናት ታከብራለች፡፡ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በሚያከብረው የመውሊድ በዓል ውስጥ ስለሀገር ሰላም ሲሉ በቀበሮ ዋሻ ውስጥ የሚያከብሩ ኩሩ እና ጀግና ኢትዮጵያውያን ትናንት በታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በተግባር አግኝተናል፡፡
ፍራሽ ካቃጠላቻው እና ምንጣፍ ከጎረበጣቸው ቅንጡዎች በተፃራሪ ስለሀገር እና ሕዝብ ደኅንነት ሲሉ መውሊድን ካርቶን ዘርግተው እና ቅጠል ጎዝጉዘው “አላሃምዱሊላሂ” እያሉ የሚያከብሩ ኢትዮጵያውያንን ተመልክተናል፡፡
የዛሬን ፌሽታ ሳይሆን የነገን ደስታ የሚያልሙ፣ ባጡት ጊዜያዊ የበዓል ፍቅር ሳይሆን በሚያተርፉት ዘለዓለማዊ የሕዝብ ክብር የሚደሰቱ፣ ከራሳቸው በላይ ሊሰውለት የሚወዱ ሕዝብ እና ሀገር ያላቸው ወታደሮች መውሊድን በጋራ ከሌላ የሃይማኖት ተከታይ ጓዶቻቸው ጋር በፍቅር እና መተሳሰብ ያከብራሉ፡፡ በዚህ ሥፍራ ኢትዮጵያ ትልቁን የመውሊድ በዓል በገራሚ ጽናት እና ፍቅር ታሳልፋለች፡፡ ወታደር እምነቱም ኾነ ማንነቱ ሀገሩ ናት፡፡ ወታደር ዓላማው የሀገሩ ሰንደቅ፤ ሃይማኖቱ ሀገሩ፣ ዝማሬው የሀገሩ ብሔራዊ መዝሙር እና ኩራቱ የሀገሩ ክብር ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ብዝኃነት ውበት ከሆነበት ሀገር የወጡ ወታደሮች አንድ ዓላማ እና አንድ ግብ ኖሯቸው መመልከት ለነፍስ ሐሴትን ለሥጋ ተፍሲትን ይሰጣል፡፡ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ልዩነት ጌጣቸው እና ውበታቸው ነው፡፡ አንዱ ስለሌላው ደስታ እና ስለሀገሩ ከፍታ ሲል የሌላውን ለመቀበል ፈጽሞ አይከብደውም፡፡
መከባበር መለያው እና ጀግንነት ዓርማው ከሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል በግዳጅ ቀጣና ተገኝተን መውሊድን አብረን እያሳለፍን ነው፡፡
መውሊድ በምሽግ ውስጥ ምን ስሜት አለው? ከሠራዊቱ መካከል የተወሰኑትን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጋዜጠኞች ቡድን አነጋግሯል፡፡
መውሊድን በግዳጅ ቀጣና ውስጥ ኾኖ ማክበር ለእኔ አዲስ አይደለም ያለን ሻለቃ ሐሰን ክብረት ነው፡፡ ለእኔ አዲስ የሆነው ነገር በአሸባሪው እና በወራሪው የትህነግ ቡድን ግፍ እና መከራን የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ወቅት መውሊድን ማክበሬ ነው ይላል፡፡ ምንም እንኳን ዛሬ በግፍ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው፣ በጭካኔ ወንድም፣ እህት እና ቤተሰቦቻቸውን አጥተው መውሊድን የሚያሳልፉ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ማሰብ ከባድ ነው ያለው ሻለቃ ሐሰን ይህ የሚቀየርበት እና ሽብርተኛው ትህነግ የእጁን የሚያገኝበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብሎናል፡፡
ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም አቅጣጫ አንድ ዓላማ አሰባስቧቸው በዓልን በጋራ የሚያከብሩት መከላከያ ውስጥ ነው ያለነው ደግሞ ሃምሳ አለቃ አሕመድ ዑመር ነው፡፡ ከቤተሰብ በላይም ከተለያየ አካባቢ ከመጡ ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ አከብራለሁ ያለን ሃምሳ አለቃ አሕመድ የዘንድሮውን የተለየ ያደረገው በግዳጅ ቀጣና ውስጥ ኾነን መውሊድን ማክበራችን ነው ብሎናል፡፡
አሸባሪው እና ከሀዲው የትህነግ ቡድን በኢትዮጵያውያን ላይ በከፈተው ወረራ በርካታ ወገኖች ጉዳት ደርሶባቸዋል የሚለው ሃምሳ አለቃ አሕመድ የሽብር ቡድኑን ከኢትዮጵያውያን ጫንቃ ለማውረድ ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኞች ነን ብሎናል፡፡
ለሕዝብ ሰላም ሲባል ራስን አሳልፎ ከመስጠት የዘለለ ደስታን የሚሰጥ በዓል የለም ያለን ደግሞ አስር አለቃ አሕመድ ፀጋየ ነው፡፡ የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ሕዝብ መጎዳቱ አሳዛኝ እንደሆነ ነው አስር አለቃ አሕመድ የገለጸው፡፡ አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ከቤተሰብ ተለይቶ መውሊድን በግዳጅ ቀጣና ማክበሩ የተለየ ስሜት እንደፈጠረበት ነው የተናገረው፡፡
መሠረታዊ ወታደር አደም አፍራሳ መውሊድን በግዳጅ ቀጣና ውስጥ ማክበሩ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት ገልጾ የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕልውና ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ሲደርስ በዓልን ከሕዝብ ጋር እንደምናከብር እምነት አለኝ ነው ያለው፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መልካም የመውሊድ በዓል እንዲሆን ምኞታቸውን አስተላልፈው ሕዝቡ ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ከፀጥታ ኀይሉ ጋር በመሆን ስላሳየው ደጀንነት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ፋኖ ተሠማራ ፋኖ ተሠማራ እንደ ሆቺ ሚኒ እንደ ቼጉቬራ!❞
Next article❝ነብዩ መሐመድ የሚወዷትን ሀገር እንውደዳት፤ እናክብራት❞ ፕሮፌሰር አደም ካሚል