❝ፋኖ ተሠማራ ፋኖ ተሠማራ እንደ ሆቺ ሚኒ እንደ ቼጉቬራ!❞

1430

ሰልጥን፣ ከሰለጠንክ ታጠቅ፤ ከታጠክ ዝመት! ከዘመትክ መክት፣ አጥቃ!

ጥቅምት 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ)ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርጎ አሸባሪው ትህነግ ወረራ ከፈፀመ ወራት አልፈዋል። ሺዎችን ለውጊያ ሌሎች ሺዎችን ደግሞ ለዘረፋ አሰማርቷል። በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈፀምም ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ፈፅሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል። ይሔ ሁኔታ ያንገበግባል፤ ይቆጫል አልፎም ረፍት የሚነሳ ጥቃት ነው።

እናም ለምን ጠላት እስካሁን ወገኔን እያሠቃየ ውሎ እንዲያድር አቅም ሊያገኝ ቻለ? እኔስ ምን ላድርግ ብሎ መቆጨት ያስፈልጋል። ተርፎት የሚያካፍለው ወገን እየተገደለ፣ የዕለት ጉርሱን እየተጠነቀ፣ ንብረቱን እየተዘረፈ ቤቱ እየተቃጠለ፣ ንብረቱ እየወደመ እኔ የተለመደ ህይወቴን እንዴት አቋርጨ ለወገኔ ልድረስ ብሎ በቆራጥነት መነሳት የግድ ይላል።

❝ፋኖ ተሠማራ ፋኖ ተሠማራ፣
እንደ ሆቺ ሚኒ እንደ ቼጉቬራ!❞
የ20ኛው ክፍለ ዘመን አብዮተኛ ቼጉቬራ በሙያው ሐኪም ነው። ዜግነቱም አርጀንቲናዊ። በሙሉ ስሙ ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ እየተባለ የሚጠራው ይህ ቆራጥ ሰው በዓለም ዙሪያ በነፃነት ታጋይ ወጣቶች ልቦና ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው።

ታዲያ ይህ ሰው የሕክምና መሳሪያውን ጥሎ ቦንብና ጠመንጃውን ለመታጠቅ የተገደደው ለምን ይሆን? ቼጉቬራ ነፍጡን ለማንሳት የተገደደው ጭቆና የሚፈፀምባቸውን፣ የተገፉትን፣ ፍትሕ የራቃቸውንና የተበደሉትን ንጹሐን ህይወት ለመታደግ በመወሠን ነበር። የዩኒቨርሲቲ መምህርነቱን ትቶ ጭቁኖችን ኩባዊያንን ነፃ ለማውጣት ወደ ትጥቅ ትግል ከእነፊደል ካስትሮ ጋር የገባው። ቼ ከእልህ አስጨራሽ ጦርነት በኋላ ድል አደረገ።

ቼጉቬራ ከድል በኋላ ከስልጣኑም ከሹመቱም ባይቀርበትም ሌሎች ነፃነት የሚሹ ሕዝቦች አሉና ወደዛ ማቅናትን መረጠ። ቼ ለሌሎች ሀገሮች ዜጎች ይሔን ያህል የነፃነት ዘማች የፍትሕ ጠበቃ መሆኑን ስናስብ እኛ ቤታችን ድረስ በጠላት ለተወረርነው ኢትዮጵያዊያን ምን ያስተምረናል?

የቀን ነብር ኾነን የሌሊት አንበሳ፣
እንዴት ውሎ ያድራል ጠላት በኛ ማሳ፣
ማን ያስቆመን ይሆን አብረን ስንነሳ።

አንድነት ኩራት ነው፤ ከጥቃትም ያድናል። መደራጀት ጀግንነት ነው፤ የጠላትን አንገት አስደፍቶ ቀና እንዳይል ያስችላል።

የወረረህን ጠላት ቆም ብለህ አስብ፤ ጠላትህን በእጥፍ ጨክንበት ከእንቅልፍህ ቀንሰህ አስብበት። አሁን የመደበኛው ህይወት ኑሮህን አቁምና እንደወታድር ሁን። ሰልጥን፣ ከሰለጠንክ ታጠቅ፣ ከታጠቅክ ዝመት! ከዘመትክ መክት፣ አጥቃ!

በሀብተጊዮርጊስ አበይ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article❝የመውሊድ በዓል ፈጣሪ ለሰው ልጆች ምን ሰጠን? ፈጣሪስ ከሰው ልጆች ምን ይፈልጋል? የሚለውን የምናስታውስበት፤ ይሄንንም በልዩ ልዩ መንገድ የምንገልጥበት በዓል ነው❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next articleየመውሊድ በዓል በግንባር…