❝ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች በራሷ አቅም ከመፍታት የሚያግዳት መሰናክል የለም❞ የጋምቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ማመዱ ታንጋራ

179

አዲስ አበባ: ጥቅምት 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች በራሷ አቅም ከመፍታት የሚያግዳት መሰናክል የለም” ሲሉ የጋምቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ማመዱ ታንጋራ ገለጹ።

ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ትናንት ተጠናቋል።

በምክር ቤቱ ውይይት ላይ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ከስብሰባው ተሳታፊዎች መካከል የጋምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ማመዱ ታንጋራ በአዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ ጉብኝት አድርገዋል።

በዚሁ ጉብኝታቸው ላይ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ኢትዮጵያ ችግሮቿን በራሷ አቅም ከመፍታት የሚያግዳት መሰናክል የለም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበረውን የቆየ ችግር የፈታችበትን መንገድ በማሳያነት ጠቅሰው፤ የራሷን ችግር የማትፈታበት ምንም አይነት ምክንያት የለም ነው ያሉት።

የአፍሪካ ሀገራት ያሉባቸውን ችግሮች በራሳቸው የመፍታት አቅማቸውን ሊያዳብሩ ይገባል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ሌሎች በእኛ ጉዳይ ከእኛ በልጠው ስለ ራሳችን ሊነግሩን አይችሉም” ብለዋል።

በአፍሪካ ጉዳይ ከአፍሪካዊያን በላይ መፍትሔ የሚያመጣ አካል ሊኖር አይችልም የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

“አፍሪካን ለመለወጥ ቆርጠው የተነሱ መሪዎች አሏት፤ አፍሪካ በትክክለኛው መንገድ እየተጓዘች ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያና ጋምቢያ ያላቸው ግንኙነት በጣም ጥሩ የሚባል ነው” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸው ስምምነቶች ከዚህ ቀደም መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚደርስ ያላቸውን እምነት በመግለፅ ስምምነቶቹን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ በፈጣን ልማት ላይ መሆኗንና የመላ አፍሪካዊያን ሁለተኛ ቤት አዲስ አበባም ትልቅ ለውጥ ላይ ትገኛለች ብለዋል ዶክተር ማመዱ።

ኢትዮጵያና ጋምቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1965 ሲሆን ጋምቢያ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከፍታለች።

ኢትዮጵያ ደግሞ ሴኔጋል ባላት ኤምባሲ ከጋምቢያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን ሁለቱ ሀገራት ንግድን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራርመዋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ኢትዮጵያን ታድጌ ካልተሠራ ቤቴ መቼ ወልዳኛለች መክናለች እናቴ” ሊቀ መኳስ ያለው አዳነ
Next article❝የመውሊድ በዓል ሲከበር በአሸባሪው የትህነግ ወረራ የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን በመርዳት፤ ሀገራችን አሁን ካለችበት ፈተና እንድትወጣ ዱዓ በማድረግ እንዲሆን ጥሪየን አቀርባለሁ❞ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋየ