
የክልሉ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ያወጣው መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል።
የጀመርነውን የህልውና ዘመቻ ሳንቋጭ ሀሳብና ተግባራችን ከዓላማና ግባችን መንቀል ከፍተኛ ዋጋ እንዳያስከፍለን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የህልውና ዘመቻው ተገደን የገባንበት እንደሕዝብ የመኖርና ያለመኖር መጻኢ እጣፋንታችን የምንወስንበት እንጂ የፓለቲካ ማሳለጫ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ፓለቲካም ይሁን ስልጣን ሕዝብና ሀገር ከመኖራቸው በኋላ የሚታሰቡ እና የሚመጡ ናቸው። ያለሕዝብና ያለሀገር የሚኖር ፖለቲከኛም ሆነ ስልጣን አይኖርም። አይታሰብምም።
በአማራ ሕዝብ ላይ እያንዣበበ ያለው የህልውና አደጋ፤ አደጋ ብቻ አይደለም። ለክልሉ መንግሥት ይሁን የአማራ ሕዝብ “ከህልውና ዘመቻው” የሚቀድም አንዳች አጀንዳ አይኖረውም። በሴራና በተንኮል ጥርሱን ነቅሎ ያደገው አሸባሪው ቡድን የእድሜ ልክ ምኞቱና ፍላጎቱ በስውር የአማራን ሕዝብ አንገት ማስደፋት እና ማኅበራዊ እረፍት መንሳት ነበር። ይህ በሴራ ተጠንስሶ በሴራ ተወልዶ የኖረን ቡድን ከዘመናት ሴራና ተንኮሉ ባሻገር በግላጭ በአማራ ሕዝብ ላይ ወረራ ፈጽሟል።
በክልሉ በግልጽ ወረራ በፈጸመባቸው በሰሜን ወሎ፣ ዋግኽምራ፣ በከፊል ደቡብ እና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ቁጥሩ በውል የማይታወቅ የአማራ ሕዝብ በጅምላ ተጨፍጭፏል። ለዘመናት ለፍቶ፣ ጥሮና ግሮ ያፈራው ሀብትና ንብረቱን በወራሪው ሀይል ተዘርፏል፤ ወድሟል። የመንግሥት እና የግል አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ዘርፏል።
ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የአማራ ሕዝብ ከሀብትና ንብረቱ ተፈናቅሎ ለአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ተዳርጓል። ሕጻናት ጭምር በዚህ አሸባሪ ቡድን በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍረዋል። አሁንም የሚፈጽመው ወረራ፣ ዝርፊያና ጭካኔ የተሞላበት ጅምላ ጭፍጨፋው እንደቀጠለ ነው። ለዚህ አሸባሪና ወራሪ ቡድን ጊዜ በተሰጠው ቁጥር ችግሩና ጥፋቱ ከዚህም የከፋ ይሆናል።
ከጦርነት ቀጣናው ባሻገር ባሉና አማራ በሚኖርባቸው በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ ክልል ማንነትንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ግድያና መፈናቀል የሚመነጨው ከዚሁ አሸባሪ ቡድንና የእርሱ ተላላኪ ባንዳዎች መሆኑን መናገር ደግሞ ለቀባሪ ማርዳት ነው። ዛሬም ሆነ ትናንት በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚፈጠሩ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጅምላ ግድያዎች እና ግጭቶች ተዋናይ፣ አጋፋሪውና መሪው ከዚህ የጥፋት ቡድን የሴራና ተንኮል መንገድ የሚመነጩ እና የተቀዱ ናቸው።
አሸባሪው ትህነግና ግብረ አበሮቹ ከኢትዮጵያ ምድር እስከወዲያኛው እስካልተነቀሉ ድረስ የአማራ ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህልውና በጽኑ መሰረት ላይ አይቆምም። ከዚህ አኳያ የአማራ ሕዝብ ህልውናም ሆነ የኢትዮጵያ ትንሳኤ የሚረጋገጠው ትህነግ መቃብር ላይ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም።
ስለሆነም በአሸባሪው ቡድን እኩይ ተግባር ምክንያት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ በጋራ መረባረብ ይኖርብናል። የሰሜን ጎንደር፣ የሰሜን ወሎና የዋግኽምራ ሕዝብ ከወራሪው ቡድን ነጻ ለማውጣት በሚደረገው ትግል መሳሪያ ያለው በመሳሪያው፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ትርፍ ሀብትና ንብረት ያለው በገንዘቡ፣ ሐሳብ ያለው በሐሳቡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ከሚሊሺያና ፋኖ ጎን በመሰለፍ የአሸባሪውን ቡድን ግብዓተ መሬት ማረጋገጥ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
ምክንያቱም የአማራ ሕዝብ ህልውናም ሆነ የሀገራችን ሰላም የሚረጋገጠው በአሸባሪው ትህነግ መቃብር ላይ ነው!
