
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔርን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዚጎችን ሕይዎት ሲያናጋ ቆይቷል፡፡ በርካታ ዜጎችን ቀጥፏል፣ አካል አጉድሏል፣ ሀብትና ንብረት አውድሟል፡፡ አሁንም ዜጎች ተረጋግተው እንዳይኖሩ እያደረገ ነው፡፡
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኀላፊ ባምላክ ይደግ (ዶክተር) ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት የጀመረው በባንዳዎች አማካኝነት በጣልያን ወረራ ዘመን እንደሆነ ተናግረዋል። በወቅቱ ጣልያን የአማራ ሕዝብ በሚኖርበት አካባቢ ሀገር ለመግዛትና በሰላም ለማደር የሚያስችል ጊዜ እንዳያገኝ ሆኖ ነበር፡፡ አርበኞቸ በከፍተኛ ተጋድሎ ቁም ስቅሉን ያሳዩት ነበር፡፡ ጣልያን በቆዬባቸው ዓመታት አማራን ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ለመለያዬት ሠርቷል ነው ያሉት፡፡
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግም በጣልያን ዘመን የጀመረውን የመከፋፈል የባንዳነት ተግባሩን በአገዛዝ ዘመኑ ማስቀጠሉን ነው ያብራሩት፡፡ አሸባሪው ትህነግ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የመከፋፈሉን ሂደት በመላ ሀገሪቱ ማስፋቱንም አንስተዋል፡፡ ትህነግ የመከፋፈል ሴራውን መዋቅር አዘጋጅቶ ማስቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ ጋር ተጋብቶ፣ ተዋልዶ የሚኖር እንደሆነ የተናገሩት መምህሩ በአማራ የኢትዮጵያዊነት እሴትና አኗኗር ሀገር አፍራሹ አሸባሪው ትህነግ ደስተኛ ባለመሆኑ ይህን እሴት ለማጥፋት መጣሩን አስረድተዋል፡፡ የአማራ እሴቶች በኢትዮጵያ ላይ እንደ መልካም ምልክት በመሆናቸው መልካምነቱን እና ኢትዮጵያዊነቱን ለማጥፋት በየዘመናቱ ጠላቶች እንደበረከቱበትም ተናግረዋል፡፡
አማራ እሴቱን፣ ባሕሉን እና ቋንቋውን ሌሎች ወደውት የሚጠቀሙበት ነው ያሉት መምህሩ እሴቱ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ የእርሱን ታሪክ ለማጥፋት ነው ጠላቶች የሚበረቱበት ብለዋል፡፡
ለውጥ በአንድ ጊዜ አይመጣም፣ ለውጥ ለመምጣት ተቋማትን መለወጥ ይገባል፣ የሚገነባው ተቋምም ማኅበራዊ እሴት ላይ የተመሠረተ መሆን መቻል አለበት ነው ያሉት መምህሩ፡፡ ተቋማትን የሚመሩ ሰዎችም የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የማኅበረሰቡን ሥነ ልቦና ያማከለ ተቋም ሊገነባ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ተቋማት የሕዝቡን ሥነ ልቦና እና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተደራጂተው ወደ ተግባር ባለመግባታቸውም ከአሁን በፊት የነበሩት ችግሮች መቀጠላቸውንም ነው ያስረዱት፡፡ አዲሱ መንግሥት ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ አሠራሮችን ሊተገብር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የፖለቲካ መሪዎችም ቅንነትን ተላብሰው በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሞትና መፈናቀል ማስቆም እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
የአሸባሪውን ትህነግ ተልዕኮ በሚፈጽመው ሸኔ ላይም የተጠናከረ የህልውና ዘመቻ እርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ከሞት መታደግ ይገባል ነው ያሉት። አሸባሪው ሸኔ ተልዕኮ ሰጭው ትህነግ ሲጠፋ ይጠፋል በሚል አስተሳሰብ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ችግሮቿን ለማቅለል ዲፕሎማሲ ላይ መሥራት እንደሚገባትም ገልጸዋል፡፡
ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታትም ወጣቶች ላይ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ እንደ ሀገር ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ከተፈለገ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ መሥራት እንደሚገባም ነው ያመላከቱት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
