“የጠላቶቻችን ክፉ ምኞትና ስውር ሴራ ከትግላችን ሊገታንም ሆነ ህዝባችን ሊያንበረክክ አይችልም” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

343

የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ምድር ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ ዘርን መሰረት አድርገው በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሁሉ ኢትዮጵያ እንደ ህዝብና እንደ ሀገር በአንድነቷ እንዳትቀጥል ሴራዎች እየተመረቱ ሲተገበሩ ኑረዋል።

በስሁት ትርክትና ስሁት ፖለቲካዊ ብያኔ ላይ በመመስረት ነገድ በነገድ ላይ በጠላትነት እንዲነሳ፤ አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ አድርጎ በማሳየት ኢትዮጵያ ሀገራችን አንድነቷን አጥታ የእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎች መጫዎቻ እንድትሆን ታልሞ፤ ለዚህ ተግባር ዓላማ ፈጻሚ ተመርጦና ተፈጥሮ ሲሰራ ኑሯል።

የአማራ ህዝብ አንዱ የሀሰተኛው ትርክትና ስሁት ፖለቲካዊ ብያኔ ሰለባ የመሆኑ መሰረታዊ ምክንያት የኢትዮጵያ ዘለዓለማዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለመበተን ካላቸው ክፉ ምኞትና ሥውር ሴራ የመነጨ ስለመሆኑ ለበርካቶች ገሃድ የወጣ ሀቅ ነው፡፡

የትኛውም የማንነት ልዩነት ሳይገድበው ተከባብሮና አንድ ህዝብ ሁኖ በኖረው ኢትዮጵያዊ መካከል ነገድና ጎሳ ተለይቶ አንድ ወይም የተወሰኑ ብሔረሰቦች የጥቃት ዒላማ ሲደረጉ ከኢትዮጵያዊ እሴታችን ባፈነገጠ መንገድ አንዱ በአንዱ ላይ በጠላትነት እንዲነሳ ሲደረግ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ስለሚታወቅ ነው።

የዚህ ክፉ ምኞትና ስውር ሴራ ጠማቂ እና የዘር ስካር ፈብራኪዎቹም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና የብልጽግና ግስጋሴው የሚያስጨንቃቸው፤ ጥቅማቸው የተቋረጠባቸው የአድማስ ማዶዎቹ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች እንዲሁም ተላላኪያቸውና ተልእኮ አስፈጻሚያቸው ትህነግ ስለመሆናቸው ግንዛቤ ከተያዘ ሰነባብቷል፡፡

አማራን በተገኘበት ሁሉ ማኅበራዊ እረፍት መንሳትና ያለማቋረጥ ኃብትና ህይወቱንም ጭምር የመቀማት ሥራና ሴራ የሚከናወነው በአማራነቱ ተስፋ የቆረጠ፣ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ግድ የማይለው የተሰበረ ህዝብ እንዲሆን ዒላማ በማድረግ ነው።

ሁኖም ግን አማራውም ሆነ ሌላው ወንድም ብሔር ጠላት አለኝ እንዲልና የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት እንደ ሀገር እንዳይቆም የሚደረገው ሴራ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልጽ ከሆነ ቆይቷል።

ስለሆነም ከአማራም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች ስደትና ሞት ጀርባ ትህነግ ስለመኖሩ አጠራጣሪ ሆኖ አያውቅም፡፡

አሁንም ቢሆን በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በአማራዎችም ሆነ በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በራሱ በትህነግና የትህነግን አስተሳሰብ ሳያላምጡ በዋጡ ተከፋይ ተላላኪዎች የሚደረግ ሲሆን አንድም በሚያገኟት አጋጣሚ ሁሉ መንግሥት የለም የሚል የተሳሳተ የቀቢጸ ተስፋ መልእክት ለአለቆቻቸው ለማስተላለፍ አንድም የህዝባችን አንድነት አደጋ ላይ በመጣል ኢትዮጵያን ማፍረስ ዓላማ ያለው ነው።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የተፈፀመው ጥቃት ያረጋገጠው እውነታም ይኸው ነው፡፡

አሸባሪው ትህነግ በወረራ በያዛቸው የክልላችን አካባቢዎች ከሚፈጽማቸው ግድያዎች በተጨማሪ ክልልና ቋንቋ ቀይሮ በወኪሎቹ የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ታጣቂዎች አማካኝነት በህዝባችን ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶችን የመፈጸሙ ምክንያት አማራን ከሌላ ብሔር ጋር በማጋጨት ወይም ኦሮሞን ከሌላው ብሔር ጋር ጠላት በማድረግ የህዝባችንን ኃይልና ትኩረቱን በማሳሳት ትህነግ በወረራ በያዛቸው የአማራ ቦታዎች ላይ ቆይታውን ለማራዘም የሚችልበትን እድል ለማግኘት ካለው ከንቱ ተስፋ የመነጨ ነው።

ይህ እውነታ የተገለጠለት አማራ ደግሞ ትኩረት እና ኃይሉን ሁሉ የአብዛኛው የደኅንነታችን ሥጋት ምንጭ በሆነው ትህነግ ላይ ከማድረግ አይዝልም፤ ትህነግ በቀደደለት ቦይ የሚፈስና ውስጣዊ አንድነቱን በማላላት ወደ ኋላ የሚመለስም አይሆንም።

ይህ እውነታ የተገለጠለት አማራ ኢትዮጵያ ከትህነግ እና ቅጥረኞቹ መጽዳቷ እውን ሆኖ ሕልውናው የተረጋገጠ ህዝብ እስኪሆን ድረስ ትኩረቱን፣ ኅብረቱን እና ኃይሉን ሁሉ ከፊት ለፊቱ በተጋረጠው ጉዞ ላይ ያደርጋል፡፡

ይህ እውነታ የተገለጠለት አማራ በመስዋእትነት የመውደቅ ዕጣ ፈንታ ቢገጥመው እንኳን ስለህልውናው ሲል የሚቀበለው ውድቀት ወደፊት የሚያራምድ እንጂ ወደኋላ የሚመልሰው አይሆንም፡፡

ስለሆነም በህዝባችን ላይ በኪረሙም ሆነ በሌላ ቦታ የተፈፀመውንም ሆነ ነገም ሊፈፀምብን የታቀደውን የጠላቶቻችንን ፕሮጀክት ለማክሸፍ የክልላችንም ሆነ የሀገራችን ኢትዮጵያን ጠላቶች መፋለም ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም በየቀኑ ከሚለዋወጠው ዓለማዊ፣ ሀገራዊ፣ ክልላዊ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታ ጋር ሊሄድ የሚችል አዋጭ የትግል ስልትን በመከተል ለአሸናፊነትና ለዜጎቻችን ሰላምና ደኅንነት መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

ከህዝባችንና ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ለፍትሕና ለህልውናችን የምናደርገውን ትግል በአሸናፊነት እንወጣለን፡፡

ድል ለአማራ!
ድል ለኢትዮጵያ!

Previous article“የንጹሃንን ሞት ማስቆም ኢትዮጵያን ማስቀጠልና መታደግ ነው” የፖለቲካ መምህር
Next articleአፍሪካውያን ዘላቂ ሰላማቸውን ለማስጠበቅ በራሳቸው የገንዘብ አቅም የሚደገፍ ተቋምን ለማጠናከር 480 ሚሊየን ዶላር ከአባል ሀገራቱ እያሰባሰበ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ገለጸ፡፡