“የንጹሃንን ሞት ማስቆም ኢትዮጵያን ማስቀጠልና መታደግ ነው” የፖለቲካ መምህር

230

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከደርግ ስርዓት መውደቅ ማግስት ጀምሮ አሸባሪው ትህነግ በግልጽ ሲያራምደው የቆዬው የፖለቲካ ስርዓት አማራ ጠል ነው፡፡ የፖለቲካ ጠንሳሹ ትህነግ ስልጣን ከያዘበት ዘመን ጀምሮ በአማራ ሕዝብ ላይ በርካታ በደሎች ተፈጽመዋል፡፡ የበደሎቹ መነሻና ቀያሽ አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ይሁን እንጂ ቦይ የተቀደደላቸው ትንንሽ ቡድኖችም አማራ ላይ በደሎችን ሲፈጽሙ ኖረዋል፤ አሁንም ችግሩ እንደቀጠለ ነው።

አሸባሪውና ወራሪው ቡድን ከስልጣን መንበሩ ከተወገደ ወዲህም በአማራ ላይ የሚደርሰው በደል አልቆመም፡፡

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለማቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር በውቀቱ ድረስ (ዶክተር) ማንነትን መሠረት ያደረገው ጥቃት መነሻው የተሳሳተ ትርክት መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡ የአማራ ሕዝብ ለዘመናት በሚኖርባቸው አካባቢዎች እንደ ሁለተኛ ዜጋ በመቆጠር ለጥቃት ዒላማ እየሆነ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የትህንግ ፖለቲካ ተመስርቶ የነበረው በጥላቻ ላይ ነው ያሉት ዶክተር በውቀቱ ጥላቻው በትውልዱ፣ በሕገ መንግሥቱና በተለያየ ሰነዶች ላይ የሰፈረ በመዋቅር የታገዘ ችግር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረው ችግር ሥር የሰደደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የችግሩ ሥረ መሠረት መዋቅራዊ ነውም ብለዋል፡፡ እስከ ቀበሌ ድረስ ስር የሰደደውን ጥላቻ መፍታት ይገባል፡፡

የመንግሥት የመጀመሪያው ተግባር የዜጎችን በሕይዎት የመኖር መብትን ማረጋገጥ ነው ያሉት ዶክተር በውቀቱ በመንግሥት ሥራ ከሕልውና በላይ የሚቀድም ነገር አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የዜጎችን ሕልውና ማረጋገጥ አልቻለም ማለት ችግሩን ማንም ይፍጠረው ማን መንግሥት ኀላፊነቱን አለመወጣቱን የሚያሳይ ነውም ብለዋል፡፡

ዜጎች መንግሥት እንዲሆን የመረጡት ሕልውናቸውን እንዲያረጋግጥላቸው መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ንጹሃን በሚሞቱበት አካባቢ ያሉ የአስተዳደር አካላት ከማንም ቀድመው ስለ ዜጎች ደኅንነት መናገር፣ የሕዝብን ችግር ተቀብሎ ችግሩ እንዳይደገም መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በንጹሃን ላይ የሚደርሰው ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ ከመንግሥት አቅም በላይ ነው ብዬ አላምንም ነው ያሉት፡፡

ዜጎችን መደገፍና ሲቸገሩ መድረስ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ሰብዓዊነት ነው፤ ኢትዮጵያን መውደድ ማለት ዜጎች ሲጎዱ መድረስ ማለት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በማንነታቸው ምክንያት የሚሞቱ ዜጎችን መርዳት ኢትዮጵያን ማስቀጠል፣ መታደግ ነውም ብለዋል፡፡ ለአማራ ወገኖች ድምጽን ማሰማት እና ሲቸገሩ መድረስም ኢትዮጵያዊነትን መታደግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ችግር በአንድ ጀንበር አይፈታም ያሉት ዶክተር በውቀቱ ንጹሃን የሚጠቁበት ቦታ ተገማችና የሚታወቁ ናቸው፣ ችግሩን መፍታት ካልቻለ ማኅበረሰቡ ራሱን የሚከላከልበትን መንገድ ማመቻቸት ትልቅ ተግባር ነውም ብለዋል፡፡

መዋቅራዊ የሆነውን የፖለቲካ ችግር ሁሉም በጋራ ሊታገለው ይገባልም ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያን ችግር ለመቀነስና የዜጎችን ሞት ለማስቆም መዋቅራዊ የሆኑ ችግሮችን ማስተካከል ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ሀገር አዲስ ምዕራፍ የምትጀምረው ዜጎች በእኩልነት ተጠቃሚ ሲሆኑ እና ሕልውናቸው ሲጠበቅ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ለሀገሬ የተከፈለ ዋጋ እስከሆነ ዓይኔን ማጣቴ ክብሬ ነው” የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል
Next article“የጠላቶቻችን ክፉ ምኞትና ስውር ሴራ ከትግላችን ሊገታንም ሆነ ህዝባችን ሊያንበረክክ አይችልም” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ