“ለሀገሬ የተከፈለ ዋጋ እስከሆነ ዓይኔን ማጣቴ ክብሬ ነው” የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል

204
ጎንደር፡ ጥቅምት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል የዚያድባሬ መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ የውስጥ ባንዳ ጦርነት ከፍቷል። በዚያን ጊዜ ሀገር ስትደፈር “ትምህርት ለምኔ” ብለው ወታደር መኾን መረጡ፣ ስለሀገራቸውም በከፈሉት መስዋእትነት የዓይን ብርሃናቸውን አጡ። መስዋእትነት በከፈሉላት ሀገራቸው የአሸባሪው ትህነግ መራሹ መንግሥት ብዙ ተጽዕኖ ቢያደርስባቸውም እጅ ባለመስጠት ለስኬት በቅተዋል።
የዛሬ ባለታሪካችን አቶ አማረ ብዙነህ ይባላሉ። በ1953 ዓ.ም በጎጃም ክፍለ ሀገር አነደድ ወረዳ ነው የተወለዱት። ተወልደው ባደጉበት አካባቢ የቤተ ክህነት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በመቀጠልም የሦስት ሰዓት የእግር መንገድ ተጉዘው መደበኛ ትምህርታቸውን እስከ ስምንተኛ ክፍል በደብረ ማርቆስ ከተማ ተከታትለዋል።
የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍልም ጦርነት ነበር። በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ አለመረጋጋት ስለነበር አቶ አማረ የሀገር ፍቅር አይሎባቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቀሉ። ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ካጠናቀቁ በኋላም ወደ ሀማሴን አውራጃ የነበረውን የኤርትራ ግንባር ተቀላቅለው ተፋልመዋል። በግንባሩ በመገናኛ መደብ ተሠማርተው አገልግለዋል። በመቀጠልም የሞርታር አስተኳሽ ግንባር ሆነው አገልግለዋል። ጥቂት ከሠሩ በኋላም የአየር ጦር አስተኳሽ ምድብተኛ ሆነው ሠርተዋል። የዚያድ ባሬ ወራሪ ኀይል ከተመታ በኋላ በምሥራቅ ተሠማርቶ የነበረው ሠራዊት ወደ ሰሜን እንዲዛወር ተደርጓል።
በዚህ ጊዜ አቶ አማረ የነበሩበት ክፍለ ጦር ከነበረበት ቦታ ወደ ከረን እንዲያቀና ተደርጓል። በዚያ ለማስተኮስ በሥምሪት ላይ እያሉ አንዳች ነገር ተከሰተ። ነሐሴ 10/1971 ዓ.ም ከጠላት በተሰነዘረ ጥቃት የዓይን ብርሃናቸውን ተነጠቁ። ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላም የህክምና እርዳታ ሳይደረግላቸው ውለው አድረዋል። የወገናቸው ጦር ከወደቁበት አንስቶ ወደ ሕክምና የወሰዳቸውም በነጋታው ነበር።
ከደምና ከአጥንታቸው ስለተዋሃደችው ውድ ሀገራቸው በጀግንነት ብርሃናቸውን ቢያጡም አካል ጉዳተኛ መሆናቸው ከመስራት አላገዳቸውም፣ ይልቁንም ሙሉ አካል ካላቸው በተሻለ መልኩ ደስተኛ እና ስኬታማ ሕይወት አላቸው። በጉዳት ምክንያት ከውትድርና ከወጡ በኋላ ደብረ ዘይት ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ጀግኖች አምባ በማቅናት እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ ሙያ ነክ ስልጠና እየወሰዱ ቆይተዋል። ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ጎንደር በመሄድ በአካል ጉዳተኞች የክህሎት ማበልጸጊያ ተቋም ውስጥ በእደ ጥበብ አሰልጣኝነት ተቀጥረው ሠርተዋል። የአካል ጉዳተኞች ክትትል ጉዳይ ፈጻሚ ሆነውም አገልግለዋል። ቤተሰብ መስርተው ትዳራቸውን በአግባቡ መርተዋል፤ ሦስት ልጆችን አሳድገው በማስተማርም ለቁም ነገር አብቅተዋል።
አቅም በፈቀደላቸው መጠን በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች በመሳተፍ ለሀገራቸው አስተዋጽዖ እያበረከቱ ይገኛሉ። ጎንደር ከተማ በሚገኝ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወመህ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። በዚሁ ከተማ የምክር ቤት አባል እና የማኅበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባልም ናቸው።
የእሳቸው የሕይወት መርህና ጥንካሬ የሌሎች አካል ጉዳተኞች መብት እንዲከበር እና በማንኛውም ማኅበራዊ ጉዳይ እንዲሳተፉ መሠረት ጥሏል። የጎንደር ዓይነ ስውራን ሕፃናት መማሪያ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲከፈት ከፕሮጀክት ቀረጻ ጀምሮ ሠርተዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፓራ ኦሎምፒክ ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በመሆን የአካል ጉዳተኞች ስፖርት በአማራ ክልል በ1988 ዓ.ም እንዲጀመር አድርገዋል። በስፖርት ውድድር አማራ ክልልን ወክለው በመሳተፍ እና በቡድን መሪነት 23 ሜዳልያዎችን ተቀብለዋል። በዞኑ በ12 ወረዳዎች የፓራኦሎምፒክ ስፖርት ግብረኃይል አቋቁመው አካል ጉዳተኞችን በዘርፉ ለማሳተፍ እየሠሩ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜም የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ ነው የሚገኙት።
የጦር ሜዳ ዘማችና ጀብድ ፈጻሚ ሜዳልያ በኮሎኔል መንግሥቱ ኀይለማርያም ተሸልመዋል። ተቀጥረው በሠሩበት መሥሪያ ቤትም ኮከብ ፈጻሚ በመሆን ተደጋጋሚ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ይህ ከውትድርና ያገኙት ጥንካሬ መሆኑን ነግረውናል።
አቶ አማረ አሁንም ለሀገራቸው የተለየ የፍቅር ስሜት አላቸው። ሀገር ከሌለች የእሳቸው መኖር ዋጋ አልባ ነው፣ የሰው ልጆች ሕልውናም ትርጉም ያጣል። የቀድሞ የሠራዊት አባላት በከፍተኛ የጀግንነት ወኔ እና በጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ታግለዋል። የዚያ ሠራዊት አካል የነበሩት አቶ አማረ በደምና በአጥንታቸው ከተዋሐደው ኢትዮጵያዊነት እና ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት አንጻር የደረሰባቸው የአካል ጉዳት ምንም እንዳልሆነ በኩራት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብር ከፍ በማድረግ እና በሰላም አስከባሪነት ተልዕኮ ዓለም አቀፍ ዝና ያተረፈው ጠንካራ ሠራዊት በስተመጨረሻ እንዳልነበር ሆነ፤ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ የማወክ እና የማዳከም እንቅስቃሴ የነበረው አሸባሪው ትህነግ ወደ ስልጣን ሲወጣ በትኖታል። በዚህም ለቀድሞ የሠራዊት አባላት ይሰጥ የነበረውን የነፃ የሕክምና አገልግሎት እና ጥቅማ ጥቅም አቋርጧል።
እንግልት በመፍጠር አንገታቸውን እንዲደፉ፣ ጎዳና ላይ እንዲወጡ እና ብዙዎች የአዕምሮ ሰለባ እንዲሆኑም አድርጓል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት መጨረሻ መሞት፣ መበተን እና መለመን እንደሆነ አስተሳሰብን በማስረጽ ወጣቱ ውትድርናን እንዳይቀላቀል ጠባሳ ጥሏል። በወቅቱ አሽባሪው ትህነግ መራሹ መንግሥት በግል ሕይወታቸው ላይ ብዙ ተጽዕኖ ቢያደርስባቸውም አቶ አማረ እጅ አልሰጡም። ከውትድርና ያገኙትን የመንፈስ ጥንካሬ ተጠቅመው በአሸናፊነት መንፈስ ቀጥለዋል እንጂ።
አሁን ሕዝቡ የአሸባሪውን ትህነግ ሀገር የማፍረስ፣ ሕዝብን አንገት የማስደፋት፣ ሃይማኖትን የማጥፋት እኩይ ሴራውን በአግባቡ ተገንዝቧል። ሠራዊቱን በመቀላቀልም የሀገሩን ክብር ለማስጠበቅ ጠላትን እየተፋለመ ይገኛል። ኢትዮጵያን እንደ ዳቦ በመቆራረስ ታላቋን ትግራይ ለመመስረት የተጠነሰሰውን ሴራ ለማክሸፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየታገለ ነው። ይህ ትግል ሕልውናን የማረጋገጥ ትግል ነው። በደምና በአጥንት የተገኘን ክብር የማስጠበቅ ጉዳይም ነው። ኢትዮጵያውያን የጀመሩት ትግል የባንዳነት ተልዕኮን እና የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን የማምከን ጦርነት ነው። በዴሞክራሲ ሽፋን ለዘመናት የተጫነን የባርነት ቀንበር በመስበር የሕዝብን በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ሠርቶ የመብላት፣ ወልዶ የማስተማር ጥያቄን በዘላቂነት የመመለስ ሁለንተናዊ ትግል ነው።
ባለታሪካችን ትግሉን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ፣ የህልውና ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ እና ኢትዮጵያን ወደነበረችበት ኀያልነቷ ለመመለስ ሕዝቡ የጀመረውን ሁለንተናዊ ትግል አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አደራ ብለዋል። ለዚህም ወጣቱ ኢትዮጵያ በምትፈልገው መስክ ሁሉ መግባት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ-ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአሸባሪው የትህነግ ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን 188 ትምህርት ቤቶችን ማውደሙን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡
Next article“የንጹሃንን ሞት ማስቆም ኢትዮጵያን ማስቀጠልና መታደግ ነው” የፖለቲካ መምህር