አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን 188 ትምህርት ቤቶችን ማውደሙን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

107
ደባርቅ፡ ጥቅምት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን 27 ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉና 161 ትምህርት ቤቶችን በከፊል አውድሟል፡፡ አሸባሪው ትህነግ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማውደሙ ከ50 ሺህ 581 በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ ማድረጉን የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሊጋባው ዘመነ አስረድተዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ ሒሳብ አወራርዳለሁ ብሎ በከፈተው ጦርነትና በፈጸመው ወረራ ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራዎችን በሕዝቡ ላይ አድርሷል፤ ቡድኑ በርካታ ንጹሃንን ጨፍጭፏል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ አካባቢያቸው አፈናቅሏል። ኃላፊው እንዳሉት ቡድኑ የአማራ ሕዝብ ንብረት ናቸው ያላቸውን እንስሳትን እና አዝዕርትን ሳይቀር በክልሉ በወረራቸው አካባቢዎች አውድሟል፤ በርካታ ተቋማትንም ከጥቅም ውጭ አድርጓል፡፡
አሸባሪውና ወራሪው ቡድን ከአመሰራረቱ ጀምሮ አማራን ለማጥፋት እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተቋቋመ ቡድን ነው ብለዋል፡፡ ይህን ዓላማውን ለማሳካትም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ወረራ በመፈጸም በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶችን አድርሷል ነው ያሉት፡፡ አሸባሪው ትህነግ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ያወሱት ኀላፊው በሰሜን ጎንደር ዞን የትምህርት ተቋማት ላይም ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን አስረድተዋል፡፡
በተለይም በትምህርት ቁሳቁስ ላይ ያደረሰው ውድመትና የፈጸመው ዘረፋ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ቡድኑ 159 ሺህ 688 የመማሪያ መጽሐፍትን እና 3 ሺህ 25 ማጣቀሻ መጽሐፍትን ሙሉ በሙሉ አውድሟል ብለዋል፡፡ ፕላዝማዎችን፣ ኮምፒውተሮችን፣ የመማሪያ ክፍል ቆርቆሮዎችን፣ የትምህርት ድሕፈት ቤት ተሽከርካሪዎችን፣ መቀመጫ ወንበሮችን እና ጠረንጴዛዎችን ዘርፏል፤ መውሰድ ያልቻለውን ደግሞ ሙሉ በሙሉ አውድሟል ብለዋል፡፡
በዞኑ ከ34 ሚሊዮን በላይ ብር የሚገመት የትምህርት መሠረተ ልማቶችንና ቁሳቁስ አሸባሪ ቡድኑ እንደዘረፈና እንዳወደመ ኀላፊው በተለይ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት በእነዚህ የወደሙ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 41 ሺህ 764 የአንደኛ ደረጃና 8 ሺህ 817 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ከ2014 ዓ.ም የትምህርት ቅድመ ዝግጅት ውጭ እንዲሆኑ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ትምህርት ቤቶቹ ለተፈናቃይ ወገኖች መጠለያ በመሆናቸው እና በዞኑ ያለው የጸጥታ ስጋት በመምህራንና በተማሪዎች ላይ ተጽእኖ በመፍጠሩ የ2014 ዓ.ም የተማሪዎችን ምዝገባና የመማር ማስተማሩን ቅድመ ዝግጅት ሥራ ከባድ እንዳደረገው ነው ያስረዱት፡፡
ይሁን እንጂ አሸባሪው ትህነግ በዞኑ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ላይ ያደረሰውን ውድመት በተቻለ መጠን ወደነበረበት ለመመለስ፣ የቅድመ ዝግጅት ተግባሩን ለማጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ጠላትን በደመሰሰበት አግባብ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በኅብረት ወደነበሩበት ለመመለስና ልጆቻቸው የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ከፍተኛ መነሳሳት እንዳለው አቶ ሊጋባው አረጋግጠዋል፡፡
ከቡድኑ ነፃ በወጡ አካባቢዎች የሚገኙና የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም እንዲያግዝ የአማራ ክልል መንግሥት በዞኑ ያለውን ከፍተኛ ችግር ከግምት ውስጥ አስገብቶ ወንበሮችን እና ጠረንጴዛዎችን እየደገፈ መሆኑን ጠቁመዋል። በዞኑ ከአሸባሪው የትህነግ ቡድን ነፃ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲመዘገቡና ትምህርታቸውን ለመከታተል ዝግጁ እንዲሆኑ መምህራንም ከጠላት ነፃ በሆኑ አካባቢዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራቸውን አከናውነው የመማር ማስተማሩን ተግባር በከፍተኛ መነሳሳት እንዲጀምሩ፤ የአሥተዳደር ሰራተኞች የሚጠበቅባቸውን ተግባር በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ አቶ ሊጋባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ-ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሃሮ አዲስ ዓለም ከተማ በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ግድያ አወገዘ፡፡
Next article“ለሀገሬ የተከፈለ ዋጋ እስከሆነ ዓይኔን ማጣቴ ክብሬ ነው” የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል