
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሃሮ አዲስ ዓለም ከተማ የሽብርተኛው ሸኔ ቡድን በንጹሃን ላይ አሰቃቂ ግድያና ማፈናቀል እየፈጸመ መሆኑን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከስፍራው የጥቃቱ ሰለባ ነዋሪዎችን አነጋግሮ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም በንጹሃን ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ አሰቃቂ ግድያ፣ ማፈናቀል እና የሃብት ውድመት የሚያወግዝ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የጉባኤው ዋና ሰብሳቢ መልዓከሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም “የምንሰጠው የሀዘን መግለጫ ነው፤ ምክንያቱም በምሥራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ዜጎቻችን በግፍ እየተገደሉ በመሆናቸው ነው” ብለዋል፡፡ ድርጊቱም የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤን አሳዝኗል ነው ያሉት መልዓከሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም፡፡ ሥጋ የለበሰን ሰው ሁሉ ሊያሳዝነው እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገራችን ብለው ለዘመናት በሚኖሩበት ቀየ ኑሩአቸውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት ባላሰቡትና ባልገመቱት ሁኔታ ግድያ ሊፈጸምባቸው እንደማይገባም ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
መልዓከሰላም ኤፍሬም በቀጣይም ሕዝብን የሚመራ መንግሥት የመጀመሪያ ተግባሩ ሕዝብን መጠበቅ ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ መንግሥትን ካርድ በማውጣት ሲመርጠው ከግፈኞችና ከታጠቁ አካላት ይጠብቀኛል ብሎ መሆኑ ሊረሳ አይገባም ብለዋል መልዓከሰላም ኤፍሬም፡፡ ሰብሳቢው ዜጎች በግፍ በሚገደሉበት አካባቢ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችም ግፍ የሚፈጽሙ አካላትን እስከ አሉበት ቦታ ድርስ በመሄድ ሊያስተምሯቸውና ሊያወግዟቸው ይገባል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ሰይድ ሙሐመድ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን በተደጋጋሚ ጊዜ የሚፈጸመው ግድያና መፈናቀል ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡ ድርጊቱም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የሚያሻክር፣ የመንግሥትን ተጠያቂነት የሚያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ጥቃት በሚፈጽሙ አካላት ላይ አስቸኳይ ርምጃ በመውሰድ ሕዝቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖርና የሰላም ዋስትና እንዲያገኝ መሥራት ይገበዋል ብለዋል፡፡
ሼህ ሰይድ በምሥራቅ ወለጋ በየጊዜው የሚፈጸመውን ጥቃት የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በተደጋጋሚ ቢያወግዝም ድርጊቱ ተባብሶ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡ መንግሥት በሚመራት ሀገር እንዲህ ዓይነት አስነዋሪ ድርጊት ሊፈጸም አይገባም፤ በአካባቢው የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችም የንጹሃን ሞት ሊያሳዝናቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በመግለጫው ላይ የተገኙት መጋቢ ገብሬ አሰፋም በምሥራቅ ወለጋ ኪሩሙ ወረዳ በንጹሃን ላይ ግድያ እየተፈጸመባቸው ነው ብለዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት እንዳለባቸው ቀድመው መረጃ ሲያደርሱ መንግሥት ቀድሞ ሊደርስ ይገባ ነበር ብለዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ከጥቃት የተረፉ ዜጎችን የመንግሥት የፀጥታ ኃይል በአስቸኳይ በማሰማራት ከጥቃቱ ሊታደጋቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ