ከ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ ጎንለጎን ውጤታማ ዲፕሎማሲ መካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

124
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ ጎን ለጎን ከ5 የአፍሪካ ሀገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። አቶ ደመቀ፣ ከቤኒን፣ አልጀሪያ፣ ቡርንዲ፣ ላይቬሪያ፣ እና ከኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ነው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ የመከሩት።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቤኒን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ምክክር በአዲስ አበባ ኢምባሲአቸውን ለመክፈት እንደወሰኑ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስረድተዋል። አምባሳደር ዲና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአልጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ምክክር የአረብ ሊግ ስለ ህዳሴው ግድብ የያዘውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያስተካክል አልጀሪያ ግፊት እንድታደርግ መምከራቸውን አብራርተዋል።
ከቡርንዲ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋርም የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን፣ የሱዳንን እና የግብጽን ጥቅም ባስከበረ መልኩ እየተከናወነ ስለመሆኑ መነጋገራቸውን ነው አምባሳደር ዲና ያስረዱት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ከላይቤሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር የመከሩ ሲሆን የላይቤሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላይቤሪያ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ግምት ከፍተኛ እንደሆነ እና የቆየ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ አምባሳደር ዲና እንዳሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ላይቬሪያ ውስጥ ኤምባሲ መክፈት እንዳለባት እና ኢንባሲው በሁለቱ ሀገራት ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ለኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ነግረዋቸዋል፡፡
ከኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በተካሄደው ምክክርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢጋድ ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት እና የአፍሪካውያን ችግር በአፍሪካውያን መፈታት እንደሚገባውና የኢትዮጵያን ሰላም አጥብቀው እንደሚፈልጉ መናገራቸውን አምባሳደር ዲና ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ አብራርተዋል።
የአምስቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለኢትዮጵያ ቀና አመለካከት እንዳላቸው ታይቷል ያሉት አምባሳደር ዲና በውይይቱ ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልጉ ለመገንዘብ መቻሉን እና ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት እንደሆነ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ – ከአፍሪካ ሕብረት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአፍሪካ አህጉር ፍትሐዊ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት በ16 ቢሊየን ዶላር 69 ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማት እና የኢነርጅ ኮሚሽን አስታወቀ።
Next articleየአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሃሮ አዲስ ዓለም ከተማ በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ግድያ አወገዘ፡፡