
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ አህጉር ፍትሐዊ የሆነ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት በ16 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ በጀት 69 ፕሮጀክቶችን በሁሉም የአህጉሩ አካባቢ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ።
ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አፍሪካውን የኀይል አቅርቦት የማያገኙ መሆኑ በጤና እና በንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ህብረቱ የአፍሪካ የነጻ ንግድ አየር ቀጣናን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።
የኮሮና ቫይረስ በማደግ ላይ ላለው አፍሪካ መሰረተ ልማት የጎን ውጋት ሆኖ ሰለመክረሙ ህበረቱ ከሁለት ዓመታት በኋላ ባደረገው የፊት ለፊት ስብሰባ አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማት እና የኢነርጅ ኮሚሽን ከኮሮና ወዲህ ትልቁ ስራችን የሆነው በአህጉሪቱ ካሉ 16 የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ድንበራቸውን ለእንቅስቃሴ ክፍት እንዲያደርጉ ማስቻል ነበር ብሏል፡፡ ይህም ወደፊት የአህጉሪቱን ንግድ እና ትስስር ለማጠናከር እንዲጠቅም እየሰሩ መሆናቸውን ኮሚሽነሯ ዶክተር አቡዚያድ አማኒ አስረድተዋል፡፡
በኮሮና ወቅት ጥሩ የትብብር እና አፍሪካዊ መፍትሔዎች ተገኝተዋል ነው ያሉት፡፡ “ኮሮናን ለመከላከል ባቋቋምነው የአቬሽን ታስክ ፎርስ ኮሮናን ለመከላከል ጠቅሞናል፤ ዛሬ 35 የአፍሪካ ሀገራት ነጻ የአየር ቀጣና ንግድን መቀላቀላቸውን ሳበስር በደስታ ነው” ብለዋል ኮሚሽነሯ፡፡ ይህም በተለይ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ትብበር የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን በዚህ የኮሮና ወቅት የተጎዱ አየር መንገዶችን እንዲያገግሙ እንዲሁም አፍሪካውያን በተመጠነ ዋጋ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ መንግሥታት ትራንስፖርቱን ከቀረጥ ነጻ በማድረግ አገልግሎቱን ለማሳለጥ መጠየቁን ገልጸዋል፡፡
አፍሪካን በድጂታል መንገድ ማስተሳሰር አሁን ወቅቱ የሚያስገድድ በመሆኑ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ያስታወቀው ኮሚሽኑ ትምህርትን ግብርናን አፍሪካዊ መለያ ካርዶችን እና ሌሎችንም ድጅታላይዝ እንዲሆኑ እየሠራን ነው ብሏል፡፡ በመሆኑም በአፍሪካ ያለው ዝቅተኛ የኀይል አቅርቦት በጤና እና በመጠጥ ውኃ አቅርቦትን አስተጓጉሏል ብለዋል ዶክተር አቡዚያድ፡፡
አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ አቅርቦት የማያገኙ በመሆኑ ትልቅ ችግር ውስጥ እያለፉ ይገኛሉ፤ በኮሮና ወቅት እስከ 25 በመቶ የአፍሪካ የጤና ተቋማት ብቻ ናቸው ኀይል እያገኙ ያለው ይህ ደግሞ የአፍሪካውያንን ኖሮ ያቃውሰዋል ነው ያሉት፡፡
በዚህ ብቻ አይቆምም ኀይል ባለመኖሩ ንጹህ የመጠጥ ወኃ አያገኙም ይህን ለመፍታት ባለፈው ሰኔ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማስፋት የሚያስችል ፕሮጀክትን ይፋ አድርገናል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ያለውን ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ችግር ለመፍታት ኮሚሽኑ 16 ቢሊየን ዶላር መድቦ እየሠራ መሆኑን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል፡፡ በዚህም 69 ክፍለ አህጉራዊ ፕሮጅክቶችን በመሥራት ላይ ነን ነው ያሉት፡፡
“የፋይናንሰ ችግር እንዳያጋጥም ከአባል ሀገራቱ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከረጅ ተቋማት በማሰባሰብ 16 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ በጀት ወጭ እያደረግን ነው” ብለዋል። 2 ሺህ 100 ኪሎ ሜትር ባቡር መንገድ የማዘመን፣ 3 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ፈጣን መንገዶች፣ 7 ሺህ100 ኪሎ ሜትር ድልድዮች፣ የኢንተርኔት መስመሮች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ:–አንዱአለም መናን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ