
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለመላዉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1496ኛዉ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መዉሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል። 1496ኛዉ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መዉሊድ በዓል ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም ይከበራል።
የበዓሉን መከበር ምክንያት በማድረግ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ ሙሐመድ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመካ ከተማ መወለድ ለዓለም ብርሃን፣ ሰላም እና እዝነት እንዳመጣ ገልጸዋል፡፡
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ሰብዓዊ መብት መከበር፣ ዘረኝነት መጥፎ እንደሆነ፣ ከሰዎች አልፎ ስለ እንስሳት ነፍስ መጠበቅ አስተምረዋል ብለዋል፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሰዎች በሰላም እና በፍቅር አብረው የመኖር እሴታቸው ማደግ እንዳለበት፣ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት ግድ እንደሆነ፣ ስለ እምነት ነፃነት፣ ስለ ግል እና የአካባቢ ንፅህና ያስተማሩ እና ሕግጋትንም የደነገጉ የነቢዮች መጨረሻ ነቢይ መሆናቸዉን ፕሬዝዳንቱ አስገንዝበዋል።
ሼህ ሰይድ ለዓለም ብርሃን የሆኑት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መውሊድን ሕዝበ ሙስሊሙ የተወለዱበትን ቀን በተለያየ ዝግጅት በድምቀት እያከበረዉ ይገኛልም ብለዋል። ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመዉሊድ በዓል ዋና ዓላማዉ በዕለቱ የርሳቸዉን መወለድ ምክንያት በማድረግ ሕዝበ ሙስሊሙ ዘር፣ ቀለም፣ ብሐየር፣ ፆታ እና መሰል ልዩነት ሳያደርግ በጋራ በመሰባሰብ የነቢዩን አስተምህሮቶችና መልካም ሥራዎችን በማዉሳት ግንዛቤ ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡

መልካም አስተምህሮቶችን ለትዉልዱ በማስተላለፍ በፍቅር እና በደስታ የሚከበር በዓል መሆኑንም ሼህ ሰይድ ተናግረዋል። ይህ በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ እና አድማሱ እየሰፋ በዓለም ደረጃ በተለያየ ዝግጅት እየተከበረ ይገኛል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
የበዓሉ መከበር ለሃይማኖቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛልም ብለዋል ሼህ ሰይድ። በተለይም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለመዉሊድ በዓል በሰጠዉ ልዩ ትኩረት በተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎች ሀገር አቀፍ የመውሊድ በዓል መዘጋጀቱን ሼህ ሰይድ አንስተዋል፡፡ ይህም ሀገራዊ ትስስር ለመፍጠር እና የመዉሊድ በዓል ከትዉልድ ወደ ትዉልድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ሕዝበ ሙስሊሙ የዘንድሮዉን የመዉሊድ በዓል ሲያከብር በሀገራችን በተከሰቱ አስከፊ ችግሮች ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ እና ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ ዱዓ እንዲያደርግ ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሼህ ሰይድ ምክር ቤቱ በቅርቡ በምሥራቅ ወለጋ የተከሰተውን የጥቃት ድርጊት በጥብቅ እንደሚያወግዝም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ከማንኛዉም ተግባር በላይ ቅድሚያ እንዲሰጠው እና በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመዉሰድ ኀላፊነቱን እንዲወጣም ምክር ቤቱ ጠይቋል።
ሽብርተኛው ትህነግ በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ምክንያት በርካታ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ሼህ ሰይድ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡ የተፈጠረው ችግር እጅግ የሚያሳስብ፣ የሚያሳዝን እና መደጋገፍንና አንድነትን የሚጠይቅ ነዉ ብለዋል፡፡ በሽብርተኛው ትህነግ ወረራ በርካቶች መሞታቸውን እና መፈናቀላቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ በተለይ እናቶችና ሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለዉ የግፍ ግድያ እና መፈናቀል የከፋ መሆኑን ሼህ ሰይድ ገልጸዋል፡፡
በሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ለዘመናት ብዙ ሃብት ፈሶባቸዉ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የግለሰብ ንብረት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መውደማቸውንም አንስተዋል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች በየ አካባቢዉ ባለዉ አደረጃጀትና በግለሰብ ደረጃ የተጀመረዉን ልዩ ልዩ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ