
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ልማት ማኅበር የአዲስ አበባና አካባቢዋ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ምትኩ በየነ በጦርነቱ ምክንያት አርሶ አደሩ ማረስ ባለመቻሉ ሕዝቡ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ከጦርነቱ በመሸሽ በባሕርዳር፣ እብናት፣ ሰሃላ እና ደሴ አካባቢዎች ተጠልሎ እንደሚገኛ እና በየአካባቢው ሕዝብ እና በተለያዩ ተቋማት ድጋፍ እየተደረገለት እንደሆነ ገልጸዋል።
የዋግ ልማት ማኅበር በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሚገኙ አባላቱ አማካኝነት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማሰባሰቡንና ወደየ አካባቢዎቹ መላኩን ገልጸዋል። 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብሩ በጥሬ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን 97 በመቶ የሚሆነው ድጋፍ በአይነት የተሰበሰበ እንደሆነ አስረድተዋል። አቶ ምትኩ በአሸባሪው ቡድን ቁጥጥር ስር ያለው ሕዝብ በረሃብና በመድኃኒት እጦት እየሞተ እንደሆነ አመልክተዋል።

ዓለም አቀፍ ረጅ ተቋማት አሸባሪው ቡድን በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች እንዲገቡ ስምምነት ቢደረስም እስካሁን አለመግባታቸውን ነግረውናል።
የሚመለከታቸው አካላትም የሕዝቡን ሰቆቃ ተረድተው አፋጣኝና በተግባር የሚታይ ሥራ መሥራት አለባቸው ብለዋል። ሁሉም ድጋፉን እንዲያጠናክርና ለሕዝቡ ድምጽ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ