
ጥቅምት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “እኔ ለሀገሬ ምን ሠራሁላት እንጅ፤ ሀገሬ ለእኔ ምን ሠራችልኝ አትበል” የሚለው የእውቁ አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ብሂል የሚሠራው ኢትዮጵያ ውስጥ ይመስላል፡፡ የአንድ ወቅት ሥርዓት አራማጆች ተጠቅመው ሲያገሏቸው አምባገነኖችን እንጂ ሀገራቸውን የማይቀየሙ፣ ክፉዋን የማይመኙ እና እንደገና ስትፈልጋቸው ያለማቅማማት በተፈለጉበት ሁሉ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ትናንት ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ አባላት በጨለማ ዘመናቸው ጧፍ የሆኑላቸውን ኢትዮጵያውያን ገና የጨለማው ጎህ ሳይቀድ ማክሰምን ጥንት ከምስረታቸው ጀምረው ተክነውበታል፡፡ የሽብርተኛው ትህነግ አባላት ያሻገራቸውን ድልድይ ለመስበር የማይሰቀጥጣቸው፣ የወሰዳቸውን ጎዳና ለማፍረስ ሃፍረት የማይሰማቸው፣ ከውርደት፣ ከሽንፈት እና ከሞት ያተረፏቸውን ጀግኖች ዞሮው ለመንከስ ይሉኝታ እንኳን የማያውቁ አረመኔዎች ሆነው ተፈጥረዋል፡፡
በአሸባሪው ትህነግ እኩይ ተግባር በርካታ የሀገር ባለውለታዎች አዝነዋል፤ በስርዓቱ አንገታቸውን ደፍተዋል፤ እንዲሁም በባለጊዜዎች ተገፍተው ዳር ላይ ወድቀው ቆይተዋል፡፡ ምንም እንኳን የዚህ ሁሉ ግፍ እና በደል ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቢሆኑም የአማራ ሕዝብ ግን የችግሩ የተለየ ገፈት ቀማሽ ነበር፡፡

ወታደራዊው ደርግ በምዕራባውያኑ ውስብስብ ሴራ እና በኢትዮጵያውያኑ ቀድሞ አለመንቃት ምክንያቶች ከመንበረ ስልጣኑ ሲወርድ ለአፍሪካ ኩራት የነበረው ወታደር “የደርግ ወታደር” የሚል ታርጋ ተለጥፎበት እስከ ሕይዎት የከፈለው መስዋእትነት ዋጋ አጥቶ እንደተራ ነገር ሲበተን ያዘኑት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ አባላት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተበተነ እና “የደርግ” የሚል ታርጋ የለጠፉበትን የሀገር ኩራት ወታደር በጭንቀታቸው ቀንና ላሰቡት ዓላማ ለመጥራት ግን ዐይናቸውን እንኳን በጨው አላሹም ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ከጉድ ያወጣቸውን ወታደር በተለመደው ክህደታቸው ምክንያት እየደረደሩ ከሠራዊቱ ከመቀነስ ያገደ የሥነ ልቦና ልዕልና አልታየባቸውም ነበር፡፡
ይባስ ብሎ ስለሀገር እና ሕዝብ ሲሉ ድጋሜ ወታደራዊ ሙያቸውን የተቀላቀሉት ነባር የሠራዊቱ አባላት የደረሰባቸው ግፍ እና መገለል ትውልዱ መከላከያን እንዳይቀላቀል እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ምክንያት ሆኖት ቆይቷል፡፡ ይህ ድርጊት ሽብርተኛው ትህነግ የአማራ ሕዝብን ከመከላከያ ለመነጠል የተጠቀመበት ስልታዊ ሂደት እንደነበር የሚያምኑትም ብዙዎች ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሁሉ ሀገር የሕልውና አደጋ ሲገጥማት እና እገዛቸውን ስትፈልግ ያለስስት ለመስጠት የወደዱ የቀድሞ ሠራዊት አባላትን አነጋግረናል፡፡ የሀገሪቱ የቀድሞ ሠራዊት አባላት አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን የፈጠረውን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ ከወገን ጦር ጎን ተሰልፈው ሙያዊ እና ሀገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ግንባር ደርሰዋል፡፡
ሃምሳ አለቃ አድጎ ሽፈራው ለ14 ዓመታት ሀገሩን እና ወገኑን በውትድርና ሙያ አገልግሏል፡፡ አግላይ እና የአንድ ብሔር የበላይነት ሰፍኖ በነበረበት ትህነግ መራሹ ሥርዓት ውስጥ ሀገሩን በቅንነት በሙያው እያገለገለ ነበረ፤ ሃምሳ አለቃ በወቅቱ በነበረው መንግሥታዊ ሥርዓት አልበኝነት እና የአንድ ብሔር የበላይነት ምክንያት የቀረበለትን የመኮንንነት ስልጠና ለመቀበል ከበደው፡፡ የመኮንንነት ስልጠናውን አልቀበልም ያለው ሃምሳ አለቃ ምንም እንኳን በእሳት እየተፈተነ ሀገሩን ለ14 ዓመታት በሙያው ቢያገለግልም ግልጋሎትህ ሰባት ዓመት ብቻ ነው በሚል ያለጡረታ ተገለለ፡፡
ከውትድርና ሙያው ተገልሎ በተቀላቀለበት ማኅበረሰብም ቅድሚያ ማግኘት ቀርቶ ተረስቶ እንደቆየ የሚናገረው ሃምሳ አለቃ አድጎ ድጋሚ ሀገሩን በሙያው ለማገልገል ወደ ግንባር ሲዘምት “እኛ ለሀገራችን ቀብድ ካልተያዘልን አላልንም፤ አንልምም” ነው ያለን፡፡

ከአሸባሪው ቡድን አባላት ጋር በበርካታ አውደ ውጊያዎች እንተዋወቃለን ያለን ደግሞ አስር አለቃ ሰማኝ ደሳለኝ ነው፡፡ የሽብር ቡድኑ ወታደሮች በወታደራዊ ሙያ ውስጥ የአስተዳደር ሥራ እና ስታፍ መሆን መለያቸው ነበር የሚለው አስር አለቃ ሰማኝ በማዕረግ እድገት ኮርቻ ላይ ሲቆናጠጡ ግን “ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ይሉት ብሂል አይነት ነበር ብሎናል፡፡ የትህነግ አባላት ጥቅም እንጂ ሀገር መርሃቸው እንዳልነበር ድሮም እናውቃለን የሚለው አስር አለቃ ሰማኝ የሕልውና ዘመቻውን በድል በማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን እና የአማራ ሕዝብ የተጣበቀበትን የዘመናት መዥገር ለመንቀል በድጋሜ ትግሉን እንደተቀላቀለ ነግሮናል፡፡
ሌላው ዘማች አስር አለቃ ዓለምነው በለው ቅሬታው ከሥርዓት ጋር እንጂ ከሀገር ጋር አለመሆኑን ጠቅሶ ሀገር ላይ ቂም መያዝ የኢትዮጵያውያን እሴት አይደለም ብሎናል፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ ሀገርን ለውርደት እና ወገንን ለእንግልት ዳርጓል የሚለው አስር አለቃ ሰማኝ ጠላት ድጋሚ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥጋት እስከማይሆንበት ደረጃ ድረስ ለመታገል ቁርጠኛ ነን ብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከገረገራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ