
ጥቅምት 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ የተባረሩትን ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሠራተኞችን አስመልክቶ ከተለያዩ አቅጣጫዎች አስተያየቶች እየጎረፉ ነው። አብላጫው አስተያየት የኢትዮጵያን መንግሥት ድርጊት የሚያወግዝ ሲሆን ጥቂቱ ወገን ደግሞ የመንግሥትን ድርጊት የሚደግፍ ነው። ወቃሾቹም ሆኑ ደጋፊዎች፣ ይህ ነው የሚባል ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ መርህ ወይም ልማዳዊ አሠራርን ዋቢ ያደረገ ሰነድ ሳያቀርቡ በደፈናው “አይቻልም” ወይም “ደግ አደረገ” በማለት ውዥንብር እየፈጠሩ ነው። በዚህ አጭር ጽሑፍ፣ በተግባር ላይ ያሉትን ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን እና በሀገራት መካከል ለዘመናት ሲተገበር የነበረውን አሠራር እንቃኛለ፡፡
ጸሐፊው ለሰላሳ ዓመታት በተመድ ውስጥ በተለያየ ደረጃ ሲሰሩ ካካበቱት ልምድ ተነስተው ከወገናዊነት በጸዳ መልኩ በአመክንዮ ጉዳዩን ለማጥራት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1945 ዓ.ም ከ50 የማይበልጡ ሀገራት በጋራ ያቋቋሙት የራሱ ቻርተር ያለው፣ አባል ሀገራቱ በያመቱ በሚያዋጡት መዋጮ የሚተዳደርና የነዚህን ሉዓላዊ ሀገራት ፍላጎትና የጋራ ዓላማ በተግባር ለመተርጎም የተቋቋመ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ነው።
ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዓላዊ ሀገርና በፋሺዝም ላይ የመጀመርያ ድልን እንደ ተጎናጸፈች ሀገር ብቻ ሳይሆን የድርጅቱ ቻርተር ሲረቀቅ በወቅቱ የኢትዮጵያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት ታዋቂው የሶቦርን ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ አክሊሉ ሃብተ ወልድ መሪነት የድርጅቱን ቻርተር ያረቀቀች መሥራች ሀገር ናት። ከመሥራች አባላቱ ሌላ፣ ድርጅቱ ሲቆረቆር “ሀገር” ያልነበሩ፣ ዛሬ ግን ኢትዮጵያን በጸጥታው ምክር ቤት ያለመታከት የምትከሰውን ሀገር ጨምሮ 193 አባል ሀገራት አሉት። በድርጅቱ ቻርተር መሠረት ሁሉም የድርጅቱ አባል እኩል ሲሆኑ አምስቱ ግን ከሌሎች የተለየ ድምጽን በድምጽ የመሻር የቬቶ ሥልጣን ተስጥቷቸዋል። የድርጅቱ ዋና አስተዳዳሪ (በተለምዶ የተመድ ዋና ጸሐፊ) የሚባለው 193ቱ አባል ሀገራቱ በሚሳተፉበት ቀጥታ ምርጫ ለቦታው ብቁ ናቸው ተብለው ለውድድር ከሚቀርቡት ግለሰቦች መካከል ድርጅቱን ለማስተዳደር ብቁ ነው ብለው ለአምስት ዓመታት የሚቀጥሩት፣ በቀጥታ በአባል ሀገራት መዋጮ የሚተዳደር ደሞዝተኛና ለአባል ሀገራቱ ሙሉ ተጠያቂነት ያለው የሲቪል ቢሮክራት ነው።
በሉዓላዊ መንግሥታት መካከል የሚኖረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና አንድን ሀገር ወክለው ወደ ሌላ ወዳጅ ሀገር የሚላኩትን ዲፕሎማቶች ጥቅማ ጥቅሞችና አይነኬነትን ለመቆጣጠር የሚያስችል በ1961 ዓ.ም የተፈራረሙት የቪዬና ውል ሲገዛው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ወክለው ወደ ሌላ ሀገር ስለሚላኩ የድርጅቱ ሠራተኞች ጥቅማ ጥቅምና አይነኬነት የተፈራረሙት ነገር የለም። በእርግጥ የ1946ቱ የተመድ ውል በአብዛኛው ስለድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነትና የድርጅቱን ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት አይነኬነት የሚያትት ቢሆንም ስለ ድርጅቱ ሠራተኞች መብትና ግዴታ ጥቂት አንቀጾችን አካትቷል።
ስለዚህ ሰሞኑን ከኢትዮጵያ የተባረሩ የተመድ ሠራተኞችን በተመለከተ ሊጠቀስ የሚገባው ይኸው የ1946 ውል እንጅ መንግሥታት ስለሚለዋወጡት የዲፕሎማቶች መብት ስለሚያትተው የ1961 የቪዬና ውል አይደለም። በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ሁለት ዓይነት ዲፕሎማቶች አሉ።
የመጀመርያው ዲፕሎማቶች ሀገራትን ወክለው የሚመደቡ አምባሳደሮችንና ሌሎች ለተመሳሳይ ወይም የአጭር ጊዜ ተልዕኮ የሚሠማሩ ዲሎማቶችን ያካትታል። እነዚህ በደንቡ መሠረት ከሆነ እንኳን በሰላም ጊዜ ይቅርና በላኪውና በተቀባዩ ሀገራት መካከል እንኳ ጦርነት ቢከፈት የሙሉ የአይነኬነት መብት ያላቸው ዲፕሎማቶች ናቸው። ይህም ማለት የፈለገውን ዓይነት ወንጀል ቢፈጽሙም ካለ ሀገራቸው በጎ ፈቃድ ውጪ፣ ተመድበው በሚሠሩበት ሀገር ሕግ በወንጀል አይከሰሱም።
ከመቶ ሺህ በላይ ከሚቆጠሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ውስጥ ግን ሙሉ ዲሎማቲክ መብት ያላቸው ግለሰቦች 1ኛ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ፣ 2ኛ ምክትል ዋና ጸሐፊዎች እና 3ኛ ረዳት ዋና ጸሐፊዎች ብቻ ናቸው። ከዚህ ውጭ ያሉ የደርጅቱ ሠራተኞችና በየሀገሩ የሚሾሙት የድርጅቱ ተጠሪዎች ሊኖራቸው የሚችለው የዲፕሎማቲክ መብት እንደ ሀገራቱ መልዕክተኞች የሙሉ አይነኬነት ሳይሆን፣ የሙያዊ አይነኬነት ብቻ ነው። ይህም ማለት ሙያቸውን መሠረት ያደረገና የድርጅታቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴና ድርጊት ምክንያት ተቀባዩ ሀገር እንደ ጥፋተኛ ቆጥሮአቸው በሀገሪቷ ሕግ መሠረት አይቀጣቸውም ማለት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብዙ የተለያዩ ተልዕኮ ያላቸው ፕሮግራሞች እና ሰብዓዊ ጉዳዮችን የያዙ ፈንዶች ሲኖሩት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ድርጅት በስተቀር ሌሎቹ በሙሉ በየሀገራቱ ተልዕኮአቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙት አባል መንግሥታት በየዓመቱ የሚያዋጡትን ዓመታዊ መዋጮ ነው። በየሀገራቱ ያላቸው ቢሮም ሥራውን የሚያከናውነው ተቀባዩ አባል ሀገርን በማማከርና ሙሉ በሙሉ ተቀባዩ ሀገር አስቀድሞ ባስቀመጠው የልማትና የእርዳታ መርሃ ግብር መሠረት ነው።
መንግሥት አስቀድሞ ካስቀመጠው ወይም በውይይት ሂደት ከተስማሙባቸው የሥራና የአፈጻጸም መግባባት ውጪ የተመድ ቢሮ ዝንፍ ሊል አይችልም። ተመድ በተፈጥሮው ኢ-ፖሊቲካዊ በመሆኑ ድርጅቱ እንደ ድርጅት ወይም ሠራተኞቹ ከተመደበላቸው የልማት እና የእርዳታ ሥራ ውጪ፣ አልፎ አልፎ ግን በተቀባዩ ሀገር በጎ ፈቃድ መሠረት ለሽምግልና ከመጠየቅ በስተቀር በምንም መልኩ በሀገሪቷ የፖሊቲካ ሥራ ውስጥ እጃቸውን ሊከቱ ከቶ አይችሉም።
አንድ የተመድ አባል ሀገር መጀመርያ በስምምነት ቢሮውን ከፍቶ እንዲሠራ የፈቀደለትን የተመድ ድርጅት በምክንያት በድርጅቱ አሠራር ካልተደሰተ ያላንዳች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቢሮውን ዘግቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሹማምንቱን በሙሉ ሀገሪቷን ለቅቀው እንዲሄዱ ማድረግ ይችላል። ስለ ድርጊቱም ለተመድም ሆነ ለሌላ ማንም አካል ማብራርያ እንዲሠጥ ግን አይጠበቅበትም። ለምሳሌ በ2012 ዓ.ም የተካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ ከተልዕኮአቸው ውጪ ባገሬ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ብሎ የሩሲያ መንግሥት ዩኒሴፍን እና ዩኤንዲፒን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሞስኮ ያለውን ቢሮአቸውን ዘግተው ከእነሠራተኞቻቸው የሩሲያን ግዛት ለቅቀው እንዲሄዱ አድርጓል። ድርጊቱ ከማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር የሚጠበቅ ሉዓላዊ መብት ስለሆነ የሩሲያን መንግሥት ድርጊት ተመድም አላወገዘም። ሩሲያም ድርጊቷን እንድታብራራ ለመጠየቅ የደፈረ አንድም መንግሥት ወይም ድርጅት አልነበረም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየአባል ሀገራቱ ቢሮአቸውን የሚከፍተውና ሠራተኞቹን የሚልከው በሀገራቱ በጎ ፈቃድ ብቻ ነው። የታዳጊ ሀገራት መንግሥታት ለልማትም ሆነ ለእርዳታ ጥቅም ሲባል ተመድን በጣም ስለሚፈልጉ ራሳቸው አስቀድመው በሀገራቸው ቢሮአቸውን እንዲከፈቱ ዋና ጸሐፊውን ይጠይቃሉ። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርን የመሳሰሉትን ግን ቢሮ እንዲከፍቱ የሚጋብዝ ሀገር እምብዛም ነው። ለምሳሌ የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር በአዲስ አበባ ቢሮውን ለመክፈት 27 ዓመታት ደጅ ጠንቶ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነው ተሳክቶለት ሀገራዊና ቀጣናዊ ቢሮውን በአዲስ አበባ ለመክፈት የቻለው። የተመድ ቀጣናዊና ሀገራዊ ሹማምንት ወደ አባል ሀገራት ከመላካቸው በፊት ልክ እንደ አንድ ሀገር ተወካይ ዲፕሎማት የተቀባዩን ሀገር ስምምነት ለማግኘት የተመድ ዋና ጸሐፊ ወይም ተወካዩ፣ የተሿሚዉን ታሪክ፣ የሥራ ልምዱን፣ አገልግሎቱን እና የትምህርት ደረጃውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለተቀባዩ ሀገር መንግሥት ይልካል። ተቀባዩም ሀገር የተሿሚውን ማንነት አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው መንገድ ሁሉ ከመረመረ በኋላ ይስማማኛል ብሎ ከወሰነ “ተቀብዬዋለሁ” የሚል አጭር መልዕክት ለተመድ ይጽፋል። ተሿሚው ለሀገሪቷ የማይፈለግ ግለሰብ ሆኖ ከተገኘ ተቀባዩ ሀገር አብዛኛውን ጊዜ አንዳችም ደብዳቤ ለተመድ ሳይጽፍ ለወራት ይቆያል። ይህም ቆይታ የተሿሚውን ተቀባይነት ማጣት ስለሚያሳይ ተመድ እንደገና የሌላን ተሿሚ መረጃ ይልክና ሌላ ዙር ሙከራ ይጀምራል። ለተቀባዩ ሀገር የሚስማማ ተሿሚ እስኪገኝ ድረስ ሙከራው ይቀጥላል። ከዚህ አሠራር የምንረዳው ትልቅ ቁም ነገር፣ አንድ ተቀባይ አባል ሀገር፣ አንድን የተመድ ባለሥልጣን ከመሾሙ በፊት እንኳ የማይፈለግ ግለሰብ ሊያደርገው ይችላል ማለት ነው። በዚያውም ልክ፣ ተሿሚው መጀመርያ ላይ የሀገሪቱን ስምምነት ካገኘና ሥራ ከጀመረ በኋላ፣ በአንድ የሆነ ምክንያት የተቀባዩን ሀገር መንግሥት ካስቀየመ ያላንዳች መንግሥታዊ ማብራሪያ ከሀገሪቷ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲባረር ሊደረግ ይቻላል።
ይህ አሠራር በመላው ዓለም ተቀባይነትን ያገኘ የማንም ሉዓላዊ መንግሥት መብት ስለሆነ፣ ተመድም “ተሿሚዎቼ ለምን ተባረሩብኝ” ብሎ ውሳኔ የሰጠውን መንግሥት ለመጠየቅ አይችልም። በቅርቡ አንድ የተመድ የዓለም ምግብ ድርጅት ሠራተኛ ለተመድ ሥራ ብቻ የተሠጠውን ሳተላይት ስልክ ለአሸባሪው ትህነግ ቡድን ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ሠጥቶ እንዲነጋገርበት እያደረገ ነው የሚለው ፎቶግራፍ በማኅበራዊ ሚዲያ መለጠፉን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባለውን ግለሰብ ከኢትዮጵያ ማባረሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንደ ተባለውም፣ መረጃው ትክክል ሆኖ መንግሥት ግለሰቡን በርግጥ አባርሮ ከሆነ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን በተግባር የሚተረጉም ስለሆነ ድርጊቱ ትክክል ነው ወይስ አይደለም ብሎ የኢትዮጵያን መንግሥት ለመጠየቅ መብት ያለው ድርጅትም ሆነ ሀገር ሊኖር አይችልም፡፡
ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው አሠራር ደግሞ፣ አንዳንድ መንግሥታት “የማይፈለገውን ተሿሚ” አልፈልግህም ብሎ በግልጽ ደብዳቤ አሳውቆ ከማባረር ይልቅ፣ የግለሰቡን “አለመፈለግ” በቀጥታ መስመር ለተመድ ዋና ጸሐፊ ወይም ለተወካዩ “በቃል” ያሳውቅ እና ግለሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቀባዩን ሀገር ለቅቆ እንዲወጣ ይጠይቃሉ። ድርጊቱ አብዛኛውን ጊዜ “ያለ ጽሑፍ” ስለሚካሄድ፣ ስለሚባረረው ተሿሚ ብዙም አቧራ አይነሳም።
ኢትዮጵያ ይህን ዓይነት ዘዴ በሰፊው ከሚጠቀሙት ሀገሮች አንዷ ነች። የዛሬ አሥር ወር ገደማ በትግራይ ጦርነት በተጀመረ ሰሞን በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ምክትል ኀላፊ የነበረውን የሆላንድ ዜጋ ያባረረችው በዚሁ ዘዴ ነው። በጊዜው የተሿሚው መባረር በተመድ ዋና ጸሐፊና ተወካዮቹ ዘንድ ቢታወቅም፣ አሠራሩ ተቀባይ ሀገራት በሰፊው የሚጠቀሙበት የልዕልናቸው መገለጫ አካል ስለሆነ፣ ተመድም ሆነ ሌሎች ሀገራት አንዳችም ተቃውሞም ሆነ ጥያቄ አላነሱም። አንዳንድ ሀገራት ደግሞ፣ አንድን የተመድ ተሿሚ ለሥልጣን “አልፈልግህም” ብሎ በግልጽ ደብዳቤ አሳውቆ ከማባረር ይልቅ ተሿሚው ከማንኛውም የተቀባዩ ሀገር ባለሥልጣን ጋር እንዳይገናኝ ያደርጋሉ። ይህ ዓይነት የተቀባዩ ሀገር ተሿሚውን የማግለል ውሳኔ ለድርጅቱ ሀገራዊ ተልዕኮ መሳካት እንቅፋት ስለሚሆን የተመድ ዋና ጸሐፊ ወይም ተወካዩ “ያልተፈለገውን” ተሿሚ አንስቶ በሌላ ተሿሚ ይተካዋል። ይህም “የተሿሚውን አለመፈለግ” የማሳወቅ ዘዴ በብዙ ሀገራት የተለመደ አሠራር ነው።
ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ጉዳይ፣ በ1948 ዓ.ም አባል ሀገራቱ በኒው ዮርክ በተፈራረሙት ውል መሠረት፣ የተመድ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረት በተገኘበት የአባል ሀገር ግዛት ውስጥ በማንኛውም ጊዜና ቦታ አይነኬ ነው። የተመድ ሠራተኞች ግን፣ የሀገሪቱ ሕግ በሚያዘው መሠረት አድልኦነት በሌለበት መልኩ ተገዥ ሊሆኑ ግድ ይላቸዋል፤ ለምሳሌ በየኬላው ላይ የግል ዕቃዎቻቸው ሊፈተሹና ሊበረበሩ ይችላሉ፤ ሠራተኞቹ የሚጓዙበት የተመድ መኪና ግን በተመድ ንብረትነቱ ምክንያት ዲፕሎማሲያዊ አይነኬነት ስላለው ከማንኛውም ዓይነት ፍተሻ ነጻ ሲሆን፣ የተመድ ሠራተኞች ግን ሙያዊ አይነኬነት ብቻ ስላላቸው፣ ሊፈተሹና ሊበረበሩ ይችላሉ ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ሰሞኑን ስላባረረቻቸው ሹማምንት ጉዳይ ሁለት ነገሮችን ብቻ ማንሳቱ በቂ ነው። የመጀመርያው፣ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የተመድ አባል ሀገር በማንኛውም ደረጃ በኢትዮጵያ ተመድበው የሚሠሩ የተመድ ሹማምንትን ያላንዳች ማስጠንቀቂያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግዛቷን ለቅቀው እንዲወጡ የማድረግ ሉዓላዊ መብት አላት። ስለ ድርጊቷም ለማንም ሀገር ሆነ ድርጅት ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ የለባትም። በዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል መሠረት፣ ማንም ሀገር ወይም ድርጅት ማብራሪያ ሊጠይቅ ወይም ድርጊቱን ሊያወግዝ አይችልም። የተመድ ሹማምንቶቹ ያደረሱት በደል ምን ያህል እንደሆነ የሚያውቀው መንግሥት ብቻ ስለሆነ፤ ከዳር ሆነን ያደረሱትን ጥፋት በውል ሳናውቅ ዝም ብሎ “ይሻላል” ወይም “አይሻልም” ብሎ ለመሞገት ግን የሚቻል አይደለም።
ባይሳ ዋቅ-ወያ ከጀኔባ እንደከተበው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m